በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው:: እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች::
+ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር:: ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ:: እሱ ክርስትና ለማስነሳት: ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ:: ሚስት ወገኖቿ ባለስልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብፅ አሳደደችው::
+ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ: ያለቅስም ገባ:: እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ:: ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ: ተጠመቀ:: ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ: ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር::
+በዛው ልክ ደግሞ ገና በ20 ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል: በውበቱም ደመ ግቡ: በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር:: ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት:: እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል::
+ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም:: ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው:: እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል::
+የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ" አላቸው:: እነርሱ ግን ተሳለቁበት:: ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ:: በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው::
+አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ:: ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርበቧቸው ተመለከተ:: በስመ ሥላሴ አማትቦ: በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው:: የዘንዶውም ርዝመት 24 ክንድ ነበር::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ: ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው:: እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ: ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው::
+ክርስቶስ ተክዶ: ጣዖት ቁሞ: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው: የክርስቲያኖች ደም ፈሶ: ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ:: እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው:: የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ: ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ::
+ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ:- "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ: ወእሠውዕ ሎቱ-እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ: ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ::" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ:: ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት::
+በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት:: እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውሃ አደረገው:: ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ:: እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና: ታገሠ::
+በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ: ያጻፈ: ያነበበ: ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::
+በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ:: ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል:: እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል::
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:
Post a Comment