ቅድስት በርባራ
🌹 ቅድስት በርባራ ማናት?
🌹 ቃልኪዳኗስ?
🌹 ዐበይት በዓላቶቿስ መቼ ይታሰባሉ?
🫴 እኒህን ጥያቄዎች፦
በስሟ የምንማጸን፤ በስሟ ጽዋ የምንቃመስ፤ ዝክሯን የምናዘክርና በዓላቶቿን የምናከብር ቤተሰቦች ልናውቅ ይገባል።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፨
ታኅሣሥ 8 በዓሏ የሚከበረው፣ ቃል ኪዳኗ ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው፣ የ15 ዓመቷ ሰማዕት የቅድስት በርባራ እና የቅድስት ዮልያና ድንቅ ታሪክና ገድል በአጭሩ፨
(ከገድለ ቅድስት በርባራ የተወሰደ)
❖ የተቀበለችው ቃል ኪዳን ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው በመላው ዓለም ከጥንት ጀምሮ የምትታወቀው ከ273-306 ዓ.ም የነበረችው ሰማዕቷ ቅድስት በርባራ
✨ በተለምዶ ቅድስት አርሴማ የምንላት ሥዕል የቅድስት በርበራ ሲሆን ለመለየትም በሥዕሏ ላይ Αγία Βαρβάρα (ቅድስት በርባራ) የሚለውን ጽሑፍ መመልከት ይቻላል። ✨
ቅድስት በርባራ (ባርባራ) ዘኒቆምድያ {Αγία Βαρβάρα, Great Martyr Barbara} ከ305-311 በነገሠው በከሓዲው መክስምያኖስ (emperor Maximian) ዘመነ መንግሥት መስፍን የነበረው የዲዮስቆሮስ ልጅ ናት።
እናቷ በልጅነቷ ስለሞተች እና እጅግ ውብ ስለነበረች ሰው እንዳያያት ጣዖት አምላኪ የነበረ አባቷ ከከተማ ውጪ ለርሷም ለብቻዋ ሰገነት ያለው ማረፊያ ታላቅ ሕንፃ አሠርቶላት አንድ አረማዊ (ጣዖት አምላኪ) መምህር ብቻ ወደርሷ እንዲገባ አደረገ።
ያሠራላት ሰገነት ከፍ ያለ ስለነበር አበባዎችን ይልቁኑ በምሽት የሚያበሩትን ከዋክብት የምሽቱ አስደናቂ ግርማ እየተመለከተች መደነቅ ጀመረች። በዚህ ጊዜ እነዚህ የአባቷ ጣዖታት አስደናቂ ዓለማትን እንደማይፈጥሩ መረዳት ጀመረች። በቤቷ ውስጥም ካሉ ሴት አገልጋዮች አንዴ ይህንን ጥያቄዋን አይታ የክርስቲያን መምህር ጠቆመቻት።
ይህንንም መምህር አርጋኖስ በደብዳቤ አድርጋ የነፍሷን መሻት ነገረችውና ደቀ መዝሙሩን በድብቅ ልኮ ስለ ምስጢረ ሥላሴ፣ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን ተማረች። እውነተኛውን የድኅነት መንገድ በመረዳቷ ከእስክንድርያ ወደ ሄሊዎፓሊስ መጥቶ በነበረ ካህን በድብቅ በግቢዋ ባለ መዋኛ ገንዳ ተጠመቀች።
በይበልጥም የሰማዕታትን ታሪክ በተመስጦ ታነብ ጀመር። በድንግልና ለመኖርም ከበርቴ ባሎችን እምቢ ብላ መለሰች። በድብቅም በጸሎትና በጾም ትተጋ ጀመረች።
አባቷም ወደዚኽ ሕንጻ በገባ ጊዜ ልጁ ያሠራችውን አይቶ ዐናጺዎችን ሲጠይቃቸው፤ ይኽነን እንዲሠሩ ያዘዘቻቸው ልጁ መኾኗን ነገሩት። እርሱም “ለምን እንደዚኽ አደረግሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ወትቤሎ አእምር ወለቡ ኦ አቡየ እስመ በሥሉስ ቅዱስ ይትፌጸም ኲሉ ግብር በእንተዝ አግበርኩ ሣልሲተ መስኮተ፤ ወዘንተኒ መስቀለ በአምሳለ ስቅለቱ ለመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይላል ርሷም “አባቴ ሆይ አስተውል፤ ልዩ ሦስት በኾነ በሥላሴ ስም ሥራ ኹሉ ይፈጸማልና ስለዚኽ ሦስተኛ መስኮት አሠራኊ፤ ይኽም መስቀል ዓለሙ ኹሉ በርሱ በዳነበት በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትኽ ተመልሰኽ የፈጠረኽን አምላክ አምልከው” በማለት ተናገረችው፡፡
🌿 የቅድስት በርባራ እና የቅድስት ዮልያና ትውውቅ 🌿
አባቷም ከርሷ ይኽነን በሰማ ጊዜ በንዴት ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ። ያን ጊዜ ሸሽታ በተአምር ለሁለት በተከፈለች ዐለት ውስጥ ገብታ ለጊዜው ብትሸሸግም በኋላ ግን ወደ አባቷ ተመለሰች። እርሱም እንድትሠቃይ ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት፤ ርሱም እየገረፈ በጊዜው አሉ በተባሉ በታላላቅ ሥቃይን ቢያሠቃያትም የባሕርይ አምላክ ክርስቶስን ግን አልካደችም።
ከዚያም ብቻዋን ወደ ወህኒ ተጣለች፤ በዚያም ኾና “ጌታዬ አምላኬ ሆይ አትተወኝ” ብላ ጸለየች፤ በእኩለ ሌሊትም የእስር ቤቱን ደማቅ ብርሃን መላው፤ “ከአንቺ ጋር ነኝና አትፍሪ” የሚለውን የአምላክን ድምፅ ሰማች፤ ከዚያም ጌታችን ቊስሎቿን ኹሉ ፈወሰላት፡፡
✨ ቅድስት በርባራ ከአባቷ ስትሸሽ አንዲት ዐለት ተከፍታ ብትደብቃት በዛ አካባቢ ያለ አንድ ክፉ እረኛ ለአባቷ ተናግሮ አስያዛት። በዚህም ቅድስቷ አዝና ብትረግመው ከነከብቶቹ ወደ ትልነት ተቀይሯል። ✨
በነጋታው ቅድስት በርባራን በማርቲያኑስ ፊት አቆሟት። ኹሉም ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደዳነችና ፊቷም እንደ ፀሓይ ጨረር ሲያንጸባርቅ ተመለከቱ። መኰንኑም “አማልክቶቻችን ስለፈወሱሽ የምስጋና መሥዋዕትን ሠዊ” አላት፤ ቅድስት በርባራም ለአገረ ገዢው “በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው የዳንኩት” አለችው፡፡
✨ ቅድስት በርባራ ከአባቷ ተከፍታ የደበቀቻት ዐለት በአሁን ጊዜ (የውስጥ ገጽታ) Village of Aboud, Palestine ✨
✨ ቅድስት በርባራን ከአባቷ ስትሸሽ ተከፍታ የደበቀቻት ዐለት በአሁን ጊዜ (የውጪ ገጽታ ከታች ካለው ምስል ይመልከቱ!) ✨
በዚያም ዮልያና ነበረችና ቅድስት በርባራን ሲያሰቃይዋት አይታ ከርሷ ጋር በክርስቶስ ስም መከራን ለመቀበል በመወሰን አብራት መከራ መቀበል ጀመረች። ሁለቱም ሰማዕታትን በምስማር ሰውነታቸውን እየወጉ ያሰቃይዋቸው ነበር። ለመዘባበት ዕርቃናቸውን በአደባባይ ሊወስዷቸው ቢሞክሩም በቅድስት በርባራ ጸሎት ጌታ መልአኩን ልኮ በአስደናቂ መጎናጸፊያ ሰውነታቸውን በብርሃን ልብስ ጋርዶታል።
በመጨረሻም ጨካኙ መኰንን ብዙ ዐይነት ሥቃይ ቢደርስባቸው እነዚኽ ቅዱሳት አንስት በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንደማይለውጡ ባየ ጊዜ አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘ።
🌿 ሰማዕትነት እና ቃልኪዳን 🌿
ከወታደሮቹ መኻከል አንዱ አንገታቸው ለመቊረጥ ሰይፉን መዘዘ። በአባቷ ወደ ተዘጋጀው ወደ መግደያው ስፍራ ይዟቸው ሔደ። ያን ጊዜ ቅድስት በርባራ እንዲኽ ብላ ጸለየች “ዘላለማዊ እግዚአብሔር ሆይ ከእኔ ሞት በኋላ እኔንና መከራዬን ለሚያስቡ ኹሉ ሥጦታኽን ስጣቸው፤ ድንገተኛ ሕመምና ብርቱ (አስጨናቂ) ሞትን በእነርሱ ላይ ፈጽሞ አታምጣባቸው” አለች፡፡
ከዚያም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ መሻቷን ኹሉ እንደሚፈጽምላት ቃል ኪዳን ሲገባላት በሰጣት ቃል ኪዳን የሚታመኑ ኹሉ ድንገተኛ ሞት እንደማያገኛቸው ቃል ኪዳን ገባላት።
በመጨረሻም አባቷ የርሷንና የባልንጀራዋ የዮልያና አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘና በ15 ዓመቷ ታኅሣሥ 8፥ በ306 ዓ.ም. አንገታቸው ተቈርጦ የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጁ፤ ቅድስት ዮልያናንም በኹለት ጡቶቿ በኩላብ ሰቅለው ሰይፈዋታል፡፡
በዚያን ጊዜ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የኾነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው። ከዚኽ የተነሣ በዓለም ባለው ሥዕሏ ላይ የመብረቅ ብልጭታ ይሣላል፡፡ ቅድስት በርባራም በዚህ ምክንያት በአማላጅነቷ ከጥንት ጀምሮ ባሉት ክርስቲያኖች ከመብረቅ አደጋና ከእሳት የምትጠብቅ እንደሆነች ይነገራል።
ያም በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በመስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ኹሉ ከርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን ኾነ። ከዚኽም በኋላ የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጪ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሯቸው። ይኽ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለ ቤተ ክርስቲያን ተቀመጠ፡፡
✨ ይኽችም ሰማዕተ ክርስቶስ ቅድስት በርባራ፥ ምእመናን ከተቀደሱ ምሥጢራት ለመውሰድ ሳይችሉ ቀርተው እንዳይሞቱ በስሟ የሚማጸኑባት ናት።
ይኽችም ሰማዕተ ክርስቶስ ቅድስት በርባራ፥ ምእመናን ከተቀደሱ ምሥጢራት ለመውሰድ ሳይችሉ ቀርተው እንዳይሞቱ በስሟ የሚማጸኑባት ናት።
በአንድ ወቅት አንድ ኢስታንሲ ላወስ የተባለ ቅዱስ መነኵሴ የሞቱ ጊዜ በተቃረበ ሰዓት ቅዱስ ቍርባን የሚያቀብለው አጣ። በቅድስት በርባራ ስምም አምላኩን ተማጸነ።
በዚህም ጊዜ ቅድስት በርባራ ልመናውን ሰምታ፥ ከኹለት ካህናት ጋር ተገለጸችለት። ከኹለቱም አንደኛው ካህን ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን አቀበለው።
📌 ከመድኃኔዓለም የተሰጣት ቃልኪዳን፦
● ስሟን የሚጠራውን፣ ለስሟ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን፣ መታሰቢያ የሚያደርገውን፣
● በስሟ በታነፀው ቤተ ክርስቲያን ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ ልዩ ልዩ የቤተ መቅደስ መገልገያዎችን የሚያመጣውን፣
● ልጁን በስሟ የሰየመውን፣ ለመድኃኔዓለም ስትል የተቀበለችውን መከራ የሚያስብ በስሟ ተማጽኖ ቢለምን እስከ 10 ትውልድ ድረስ ምሕረትን ያገኛል፤
● በስሟ ለታመነ ከድንገተኛ አደጋ፦ ከመብረቅ፣ ከእሳት፣ ከዐውሎ ንፋስ፣ ከፍንዳታዎች ይድናል።
🌿 ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት እና ሰማዕቷ 🌿
ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ቅድስት በርባራን አመስግነው በቃኝ አይሉም ነበር፤ ለምሳሌ ያህል ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ቅዱስ አርከ ሥሉስ እንዴት እንዳመሰገኗት እንይ።
🌹“ሰላም ለበርባራ ወዮልያና በፍኖተ ስምዕ እለ ቆማ፥
እለ ተጋደላ ከመ ሐራ፥
● ሙሽራቸው ክርስቶስን እስኪያገኙ ድረስ ድንግልናቸውን የጠበቁ፤ የክርስቶስ መከራ መስቀሉን የተሸከሙ፤ እንደ ጭፍሮች የተጋደሉ፤ ሩጫቸውንም የፈጸሙ፤ በምስክርነት ጎዳና የቆሙ ለሆኑ ለበርባራና ለዮልያና ሰላምታ ይገባል በማለት አወድሷቸዋል፡፡ [ተአምኆ ቅዱሳን ንባቡና ትርጓሜ ገጽ 401]
🇨🇬 አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአርጋኖን (ዘእሑድ 9፥4-6) ድርሰቱም ላይ እመቤታችንን "የአርሴማ የበርባራ...የዮልያናን በረከት እንዲያርፍብኝ ለምኚልኝ" ይላታል።
🌹“ሰላም ለበርባራ እንተ አግሀደት ሃይማኖታ፥
ወሰላም ካዕበ ለዮልያና ካልዕታ እንተ ሰቀልዋ በክልኤ አጥባታ”🌹
ዳግመኛም በሁለት ጡቶቿ የሰቀሏት የርሷ ሁለተኛ ለምትሆን ለዮልያናም ሰላምታ ይገባል በማለት የተቀበሉትን ጽኑ መከራ ጽፏል፡፡
በክልኤ ዕደው ዘሰረቁ መጽሐፈ ገድላ፥
✨ ቅድስት በርባራ እና ቅድስት ዮልያና ከእመቤታችን ጋር አባ ጊዮርጊስን ለገፉ አንድ መምህር እንደተገለጡ የአባ ጊዮርጊስ ገድል በተአምሩ ይናገራል። ✨
በእጅጉ የሚገርመው ከጥንት ዠምሮ በየክፍላተ ዘመናቱ እስከ ዛሬ ድረስ በበርካታ የዓለም ክፍሎች በቅድስት በርባራ ከሚፈነዱ የጦር መሣሪያዎች፤ ከመብረቅ አደጋና ከድንገተኛ ሞት በቃል ኪዳኗ እንደምትጠብቅ ሲታመን፤ በጣሊያን የባሕር ኀይላችን ጠባቂ (the patron of the Italian Navy.) ይሏታል።
በቃል ኪዷና በእጅጉ ከመታመን የተነሣ በጊዜያችን ያሉ በርካቶች ኀያላን ሀገራት ብሪታኒያ (Royal Artillery, RAF Armoures, Royal Engineers) በካናዳ (Explosive Ordance Technicaians) በአውስራሊያ (RNZAF Armourers) በኒውዝላንድ፤ በስፔን፣ በአሜሪካ፣ በግሪክ የቅድስት በርባራን በዓል በዐየር ኀይላቸው፣ በጦር ካምፓቸው፣ በባሕር ኀይላቸው እንደሚያስቡ ጥናቶች በግልጽ ያሳያሉ።
ቅድስት በርባራ፥ በአደገኛ ሥራ ላይ ያሉ እና ከጦር መሣሪያ ጋር የሚሠሩ ሰዎች በድንገተኛ አደጋ እንዳይሞቱ በበራቸው፣ በምሽጋቸው፣ በመሥሪያ ቦታቸው፣ በጦር አርማቸው ላይ ያስቀምጧታል፤ ይሥሏታል።
ሙሉ ገድሏን በpdf ለማግኘት👇
https://t.me/Ewnet1Nat/12037
ተወዳጆች ሆይ! ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ብቻ የምትሰሙ አትሁኑ፡፡ እነርሱን ለመምሰልም ተጣጣሩ እንጂ፡፡ ለጊዜው ብቻ የምታደንቋቸው አትሁኑ፡፡ ወደ ቤታችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ ልቡናችሁ ውሳጤም ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ፡፡
ዘወትር አስቧቸው፡፡ በልቡናችሁ ጓዳ እንዲገቡ አድርጓቸው፡፡ እናንተን ትተው ይሔዱ ዘንድ አትፍቀዱላቸው፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደሆነ ዘወትር እያያችኋቸው ትበረታላችሁ፡፡ በእምነት ትጸናላችሁ፡፡
የለበሱትን የጽድቅ ጥሩር፣ የያዙትን ምግባረ ወንጌል፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ እየተመለከታችሁ ትበረታላችሁ፡፡”
የሰማዕታቱ በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደር!
አሜን!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...
በብዙ አንባቢያን የተነበቡ
-
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን ጻድቁ አባ ጳውሊ ዲያብሎስን ገዝተውት ሳለ ብዙ የሚያስትባቸውን ምሥጢራት በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ እኔም ሐይቅ ቅዱስ እ...
-
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አርማ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በአሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንዲውል ወ ሰነ ።ከዚህ በፊት ይህ አርማ በቅዱስ ሲኖዶ...
-
ክፍል ሦስት ‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል) ‹‹ዳግመኛም ሕዝቡን፣ ቀሳውስቱን፣ ካህናቱን፣ ሊቃውንቱን እንዲነቅፉ አደርጋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ከጽድቅ ሥራ ሰንፈው ለኃጢአት ሥ...
-
በሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ ‹ቅዱሳን› ማለት ‹የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐን የኾኑ፣ የጠሩ› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና የጌትነቱ መገለጫ የኾኑ ዂሉ ቅዱሳን ይባላ...
-
የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገ...





No comments:
Post a Comment