ቅዱስ ቴዎድሮስ ማር ሰማዕት

   


   በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው:: እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች::

+ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር:: ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ:: እሱ ክርስትና ለማስነሳት: ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ:: ሚስት ወገኖቿ ባለስልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብፅ አሳደደችው::

+ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ: ያለቅስም ገባ:: እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ:: ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ: ተጠመቀ:: ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ: ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር::

+በዛው ልክ ደግሞ ገና በ20 ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል: በውበቱም ደመ ግቡ: በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር:: ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት:: እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል::

+ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም:: ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው:: እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል::

+የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ" አላቸው:: እነርሱ ግን ተሳለቁበት:: ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ:: በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው::

+አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ:: ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርበቧቸው ተመለከተ:: በስመ ሥላሴ አማትቦ: በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው:: የዘንዶውም ርዝመት 24 ክንድ ነበር::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ: ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው:: እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ: ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው::

+ክርስቶስ ተክዶ: ጣዖት ቁሞ: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው: የክርስቲያኖች ደም ፈሶ: ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ:: እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው:: የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ: ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ::

+ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ:- "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ: ወእሠውዕ ሎቱ-እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ: ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ::" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ:: ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት::

+በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት:: እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውሃ አደረገው:: ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ:: እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና: ታገሠ::

+በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ: ያጻፈ: ያነበበ: ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::

+በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ:: ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል:: እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል::

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ታቦተ ጽዮን

 


    ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፤ ይህን ለመረዳት ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልናውቅ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ /ዘፀ.፳፭፥፱/፡፡ እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋ አንድ ክንድ ተኩል፤ ቁመቷ አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከኾነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሥሎ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝ አስቀመጣቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው እንዲተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ እየተገለጠ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር በግልጽ ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡም በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር  /ዘፀ.፰፥፲፩፤ ፳፭፥፳፪-፴፫/፡፡


ወደ ምሥጢሩ ትርጓሜ ስንመለስም ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጧ የያዘችው የሕጉ ጽላትም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የእመቤታችንን ንጽሕና የሚያመለክት ሲኾን፣ በውጪም በውስጥም በጥሩ ወርቅ መለበጧ ደግሞ ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል መኾኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን በግራና በቀኝ በኩል በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ነበሯት፤ በእነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥም ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸው ነበር፡፡ ታቦቷን ለማንቀሳቀስ ባስፈለገ ጊዜ አራት ሌዋውያን ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ንሥር፣ ገጸ ላህምና ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታልና /ኢሳ.፮፥፩-፭፤ ሕዝ.፩፥፩-፲፮/፡፡ ለአማናዊቷ ታቦት ለቅድስት ድንግል ማርያምም ሰላምን የሚያወሩ፣ መልካም የምሥራችንም የሚናገሩ፣ መድኀኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም ‹‹አምላክሽ ነግሦአል›› የሚሉ፣ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ የእርሷንና የጌታችንን ስም ተሸክመው ወንጌልን ለዓለም የሚሰብኩ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን አሏት /ኢሳ.፶፪፥፯/፡፡ የስርየት መክደኛው መቀመጫው የንጹሐን አንስት፣ መክደኛው የንጹሐን አበው፣ ግራና ቀኙ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤልም የጠባቂው መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡


የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ቢኾንም ነገር ግን በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት አይቀርብም ነበር፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ አይችልም ነበር፡፡ ከዚህም የምናስተውለው አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በኾነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳዘጋጀ ያመላክተናል፡፡ ይህ ስፍራ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማመልከትም ለኃጢአት ስርየት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ እየነከረ ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ይረጨው ነበር /ዘሌ.፬፥፮/፡፡ ነገር ግን ይህ ደም ከስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ የሚገባው አማናዊው መሥዋዕት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነውና፡፡


ይህ የስርየት መክደኛ ለእኛ የሚያስተላለፈው ተጨማሪ መልእክትም አለው፡፡ ይኸውም አማናዊው መሥዋዕት ክርስቶስ መሥዋዕት ኾኖ ዓለምን ማዳኑ እንደማይቀርና መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራም በቅድስተ ቅዱሳኑ (ቤተ መቅደሱ) ውስጥ እግዚአብሔር በምሕረት በሚገለጥበት በቃሉ ማደሪያ በጽላቱ ላይ መሆን እንደሚገባው ያስገነዝበናል/ዕብ.፬፥፲፮/፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ ላይ አድሮ ‹‹ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይኾናልና በየስፍራውም ስለ ስሜ ዕጣንን ያጥናሉ፤ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤›› /ሚል.፩፥፲፩/ በማለት እንደ ተናገረው የስርየት መክደኛው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቍርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መኾኑን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሁለቱ ኪሩቤል የተባሉት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጕም ይረዳል፡፡


ታቦተ ጽዮን ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ንዋያተ ቅድሳት በተለየ መልኩ እጅግ ግሩም የሆነ ምሥጢርን በውስጧ ይዛለች፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ለመረዳትም አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር /፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፯/፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሚሆን ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሟል፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ኤልሳቤጥ ሰላምታ በሰጠቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በስማቱ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሆኖ በደስታ ዘሏል (ሰግዷል) /ሉቃ.፩፥፵፬/፡፡ ቅዱስ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እየተደሰተ ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱም ለሰው ልጆች ሆሉ የመዳናችን ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን በቃል ኪዳኗ ታቦት በኩል አስቀድሞ በዓይነ ሕሊና ስለ ተመለከታቸው ነበር፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ ታስተምራለች፡፡ በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ነው።

 

 ምንጭ፡- ማህበረ ቅዱሳን 

       በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ የተዘጋጀ

አቡነ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት

 


‹‹በጎርጎርዮስ›› ስም የሚጠሩ ብዙ እጅግ የከበሩ ታላላቅ ቅዱሳን አሉ፡፡

🎚ከእነዚህም ውስጥ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ አቡነ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ራእዩ ህቡአት፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘላዕላይ ግብፅ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ እና ሌሎችም ብዙዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ኅዳር 21 ቀን የዕረፍቱን በዓል የምናከብርለት አቡነ ጎርጎርዮስ

ገባሬ መንክራት የተባለውን ነው፡፡

‹‹ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት›› የተባለው አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ስለሚታወቅ ነው፡፡

ሀገሩ ሮም ነው በዚህም ምክንያት ጎርጎርዮስ ዘሮም እየተባለም ይጠራል፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ ብሉይንና ሐዲስን ጠንቅቆ የተማረ ሲሆን

በሌላም በኩል ሕግ አዋቂና ተርጓሚ ሊቅ ስለነበር አንድ ቀን

ለተበደለ ድኃ ሊከራከርለት ሲሄድ በመንገድ ላይ ሳለ መልአክ ጠርቶት ወደ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡

ከብዙ ቆይታውም በኋላ

አረጋዊው የሀገሪቱ ኤጲስ ቆጶስ በሥራው እንዲራዳው በማሰብ

‹‹እኔን እርዳኝ፣ አንተ ተሾምና ገዳሙን አግልግል›› ቢሉት

ሹመቱንና ውዳሴ ከንቱን አልፈልግም በማለት እምቢ አላቸው፡፡

አረጋዊው ኤጲስ ቆጶስም ግድ ቢሉት ሸሽቶና ተደብቆም ገዳም

ገብቶ በተጋድሎ መኖር ጀመረ፤ ኤጲስ ቆጶሱም ካረፉ በኋላ

ማንን እንደሚሾሙ ሲመካከሩ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ

ለመነኮሳቱ ‹‹የመለኮትን ነገር የሚናገር ገዳማዊ ጎርጎርዮስን

ፈልጋችሁ ሹሙት›› ብሏቸው ተሰወረ፡፡

እነርሱም ሲፈልጉት አጥተውት ሲጨነቁ መልአኩ ድጋሚ ተገልጦ የክብር ልብሱን ሰጣቸው፡፡

መነኮሳቱም ወንጌልንና ልብሱን ከወንበሩ ላይ አኑረው እየጸለዩ እርሱ በሌለበት ሾሙት፡፡

ስሙንም ‹‹የመለኮትን ነገር በሚናገር በገዳማዊ ጎርጎርዮስ

ስም ጎርጎርዮስ›› ብለው ሰየሙት፡፡

ለእርሱም በበዓቱ ውስጥ

ሳለ የታዘዘ ብርሃናዊ መልአክ መጥቶ ‹‹ተነሥተህ ወደ እነርሱ

ሂድ፣ እነሆ በላያቸው ኤጲስ ቆጶስነት ሾመውሃልና፤ ይህም

ከእግዚአብሔር የሆነ ነው›› አለው፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስም ተነሥቶ

ሲሄድ በሌለበት በልብሱ ብቻ ሹመውት አገኛቸው፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስም ‹‹ሹመቱን አልፈልግም›› ብሎ ከብቃቱ የተነሣ በተአምር ከመካከላቸው ተሰውሮባቸው ሄደ፡፡

መልአኩም እየመራ ወስዶ ያለበትን ካሳያቸውና ለእርሱም ሹመቱ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን ነግሮት በሹመቱ እንዲጸና አድርጎታል፡፡

ከዚህም በኋላ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረገ ሲያገለግል ኖሯል፡፡

ሁለት ወንድማማቾች በጋራ የሚጠቀሙበትና ብዙ ዓሣዎች የሚጠመድበት አንድ ባሕር ነበር፡፡

እነርሱም በእኔ ይገባኛል ተጣልተው ባለመስማማት አቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ ሄዱ፡፡

አባታችንም ሊያስማማቸው ቢሉ ወንድማማቾቹ እምቢ

አሉ፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስም ባሕሩን በተአምራት አድርቆ የሚታረስ

መሬት አድርጎ ሰጣቸው፤ ወንድማማቾቹም ተካፍለው በማረስ በሰላምና በፍቅር ኖሩ፡፡

እግዚአብሔርም በአቡነ ጎርጎርዮስ እጅ ሌሎች ብዙ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን አደረገ፡፡

በዚህም ጻድቁ ‹‹ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

በስሙ አንድ ቅዳሴ አለው፣ ቅዳሴውም በዕለተ ሆሳዕና በዓል ይቀደሳል፤ ሃይማኖተ አበውና ሌሎቹም የሊቃውንት መጻሕፍት በስፋት የሚጠቅሱት ይህ ጻድቅ አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ በተወለደበትና በተሾመበት ዕለት ኅዳር 21 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡


በረከቱ ረድኤቱ ይድርብን

ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ


" ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።"

             ዮሐ. ፲፬፥፰ /14፥8/



 ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው ፊልጶስ ከገሊላ የተገኘ የቤተ ሳይዳ ሰው ነው

   ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤልን "የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል መጥተህ እይ" በማለት ከክርስቶስ ጋር አገናኝቶታል በዚህም ናትናኤል በክርስቶስ ሐዋርያ ሆኖ መመረጡን ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን። ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ከኢየሱስ ክርሰቶስ ጋር እየተከተለ ወንጌልን ተማረ ብዙ ድንቆችንም ክርስቶስ ሲፈጽም ለማየት በቃ።

   ኢየሱስ ክርስቶስን አብን አሳየን ብሎ በመጠየቁ ክርሰቶስም "እኔን ያየ አብን አየ፤ እስከዛሬ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን" ብሎ መልሶለታል (ዮሐ. 14፥9)

   ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ወንጌልን እየሰበከ ብዙዎችን ከጣኦት አምላኪነት ወደ ክርስትና አምጥቷል። ፍሬግያ፣ ሰማርያና ጋዛ በሚባሉ አከባቢዎች እየተዘዋወረ የክርስቶስን ጌትነት፣ የወንጌልን እውነት አጉልቶ አሳይቷል።

  ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ታናሽዋ እስያ በመሄድ በሄራፖሊስ ከተማ እያስተማረ ብዙዎችን በማሳመኑ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ይዘው አሰቃዩት፣ አንገላቱትም።

 ከብዙ እንግልትም በኋላ በህዳር ፲፰ /18/ ቀን በመስቀል ላይ ሰቅለውት መስዋዕትነትን ተቀበለ። የሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ምልጃና በረከት በእኛ ላይ ይደር። ጸሎቱ ከእኛ አይለይ። 

       አሜን!


ቅዱስ አባ አቡናፍር



 በገድል ከመጠመዱ የተነሣ ጥቂት የሰሌን ፍሬዎችን ብቻ እየተመገበ በበረሃ ውስጥ 60 ዓመት የኖረው ታላቁ ጻድቅ አቡነ አቡናፍር ታሪክ በትንሹ ይህ ነው፡፡

 እርሱም በእነዚህ ድፍን 60 ዓመታት ውስጥ የሰውን ፊት ከቶ አላየም፤ ይኽም ቅዱስ ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ ታላቅ አባት ነው፡፡

 ከላይኛው ግብፅ የተገኘ ሲሆን ታሪኩን የተናገረለት ጻድቁ አባ በፍኑትዮስ ነው፤ ይኸውም አባ በፍኑትዮስ ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ምንጣፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን የኖረ ነው፡፡

  ይህም ቅዱስ አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ በመመንኮስ በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋ በታላቅ ተጋድሎ ኖረ፤ ያማረ የምንኩስናውንም ሥራ በፈጸመ ጊዜ መነኮሳት ከሚኖሩበት ገዳም ርቆ ወደሚገኝ በረሃ ውስጥ ይገባ ዘንድ የከበሩ ገዳማውያንንም ይጎበኛቸው ዘንድ ለሚያነቧት ረብ ጥቅም ትሆን ዘንድ ገድላቸውንም እንዲጽፍ እግዚአብሔር አዘዘው፤ ለእግዚአብሔርም ትእዛዝ ራሱን ዘንበል አድርጎ ወደ ውስጠኛው በረሃ ገባ፡፡

  በዱር መካከልም ሲዞር ከከበሩ ገዳማውያን መካከል ብዙዎችን አገኛቸውና ዜናቸውን ተረድቶ ገድላቸውን ጻፈ፤ ገድላቸውንም ከጻፈላቸው እጅግ የከበሩ ቅዱሳን መካከል አባ ጢሞቴዎስና አባ አቡናፍር ይገኙበታል፡፡

  በአንዲት ዕለት አባ በፍኑትዮስ ወደ እርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍር አየው፤ አባ በፍኑትዮስም የሰይጣንን ምትሐት የሚያይ መስሎት ደነገጠ፤ አባ አቡናፍር ፀጉሩና ጽሕሙ ሰውነቱን ሁሉ ሸፍኖታል እንጂ በላዩ ላይ ልብስ አልነበረውም፡፡

 አባ በፍኑትዮስንም በመስቀል ምልክት ባርኮ አጽናናው፤ አቡነ ዘበሰማያትንም ከጸለየ በኋላ ‹‹አባ በፍኑትዮስ ሆይ ወደዚህ መምጣትህ መልካም ነው›› ብሎ በስሙ ከጠራው በኋላ ፍርሃቱን አራቀለት፡፡

  ከዚህም በኋላ ሁለቱም በጋራ ጸልየው የእግዚአብሔርን ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ፤ አባ በፍኑትዮስም አኗኗሩንና እንዴት ወደዚህ በረሃ እንደመጣ ታሪኩን ይነግረው ዘንድ አባ አቡናፍርን ለመነው፡፡

  አባ አቡናፍርም ታሪኩን እንዲህ ብሎ ነገረው

‹‹እኔ ደጋጎች እውነተኞች መነኮሳት በሚኖሩበት ገዳም ውስጥ እኖር ነበር፤ የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኗቸውም ሰማሁ፡፡

   እኔም ‹ከእናንተ የሚሻሉ አሉን?› ብዬ ጠየኳቸው፤ እነርሱም ‹አዎን እነርሱ በበረሃ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው፤ እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆንን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን፣ በበረሃ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው› አሉኝ፡፡

   ይህንንም ስሰማ ልቤ እንደ እሳት ነደደና ወደ ፈቀደው መንገድ ይመራኝ ዘንድ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ጸለይኩ፤ ከዚህም በኋላ ተነሥቼ ወጥቼ ስጓዝ አንድ አባት አገኘሁና የገዳማውያንን ገድላቸውን እያስተማረኝ ከእርሱ ጋር ተቀመጥኩኝ፡፡

   ከዚያም ወደዚህ ቦታ ደረስኩ፤ እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝን ይህችን ሰሌን አገኘኋት፤ በየዓመቱ 12 ዘለላ ታፈራለች፤ ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚህች ምንጭ እጠጣለሁ፡፡

  በዚህችም በረሃ እስከዛሬ 60 ዓመት ኖርኩ፤ ከአንተም በቀር የሰው ፊት ከቶ አይቼ አላውቅም›› ብሎ አቡነ አቡናፍር ጣፋጭ ታሪኩን በዝርዝር ነገረው፡፡

  ይህንንም ሲነጋገሩ የታዘዘ መልአክ መጥቶ የጌታችንን ሥጋና ደም አምጥቶ አቆረባቸው፤ ቀጥለውም ጥቂት የሰሌን ፍሬ ተመገቡ፤ ወዲያውም የአቡነ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ሆነ፡፡

  ወደ እግዚአብሔርም በተመስጦ እየጸለየ ሳለ ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፤ አቡነ በፍኑትዮስም በፀጉር ልብሱ በክብር ገንዞ ቀበረው፡፡

  ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ ወደደ ነገር ግን ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች፤ የውኃዋም ምንጭ ደረቀች፡፡

  አባ በፍኑትዮስም ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የአባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆነ፡፡

እንግድ የአባቶቻችን ታሪክ/ገድል / ብዙ ነው፡ ተነግሮም አያልቅም!

የአቡነ አቡናፍርና የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን!🙏

               "አሜን!"

ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት (ማር ሚና)

 




ህዳር 15 በምልጃው ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቀው በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው፣ በግብጻውያን ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው ስሙን ጠርተው የማይጠግቡት፣ ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ የሆነና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሚያደርግ፣ በተለይ ለታመመ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ ባለ በጎ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ የሆነው የቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ዕረፍቱ ነው።

ቅዱስ ሚናስ ከደጋግ ቤተሰቦች የተገኘ ሲኾን እናቱ ልጅ ስላልወለደች በእመቤታችን በዓል ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ተማፀነቻት ያን ጊዜ ከእመቤታችን ሥዕል አሜን የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ከዚያም ይኽነን ለባሏ ነገረችው እግዚአብሔርም የተባረከውን ልጅ በ285 ዓ.ም ሰጣት፤ ስሙንም ሚናስ ብለው ሰይመውታል ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት፡፡ እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በስፋት አስተማሩት፤ በአሥራ ሁለት ዓመቱ አባቱ ሲያርፍ ከሦስት ዓመት በኋላ እናቱ ዐርፋ ቅዱስ ሚናስ ብቻውን ቀርቷል፤ ከዚያም መኳንንቱም አባቱን ይወድዱት ስለነበር በአባቱ ፈንታ ምስፍናን እንደ ሾሙት ዜና ገድሉ ይናገራል፡፡

ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን በካደ ጊዜ ቅዱስ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገብቶ ተጋድሎን ጀመረ፤ ከዕለታት ባንዳቸው ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊልን ሲቀዳጁ ተመለከተ ከዚኽ በኋላ ወደ ከተማ ተመልሶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ መኰንኑ ቅዱስ ሚናስ በወገን የከበረ መኾኑን ያውቃልና ብዙ የሹመት ቃል ኪዳን ገባለት እርሱም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለይ እንደማይችል ነገረው።

ያን ጊዜ ብዙ ሥቃይና መከራ አደረሰበት በመጨረሻም ራሱን በሰይፍ እንዲቈርጡት አዝዞ ከክርስቶስ ቃል ኪዳን ተቀብሎ ህዳር 15 ቀን የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፤ በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ለሚጠሩት በምልጃው እጅግ ፈጥኖ ይደርስላቸዋል።

የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጅ ከሰማይ “ሚናስ ንኡድ ክቡር ነኽ፤ ከልጅነትኽ ዠምሮ የቅድስናን ሕይወት በመምረጥ ሦስት አክሊላትን ሰጥቼሃለሁ፤ አንደኛው ስለቅድስናኽ፣ ኹለተኛው ስለ ብቸኝነትኽ፤ ሦስተኛው ስለ ሰማዕትነትኽ” የሚል ድምፅን ከጌታችን ሰምቷል፡፡

ከዚያም መኰንኑ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ወደ እሳት እንዲጣል ቢያስደርግም እሳት ፈጽሞ ሥጋውን ሊነካ አልቻለም፤ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ባማሩ ልብሶች ገንዘው አኖሩት፤ የመርዩጥ አገር ሰዎች ሰራዊትን ሊያከማቹ ስለወደዱ ምልጃው ይረዳቸው ዘንድ የቅዱስ ሚናስን ሰውነት ወሰዱ፤ እነርሱም በባሕር በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያሉ አውሬዎች ከባሕር ወጥተው አንገታቸውን ወደ ሚናስ ሥጋ በዘረጉ ጊዜ ከሰውነቱ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጥላቸዋለች፤ ሰዎቹም ይኽነን አይተው በእጅጉ ተደንቀዋል፡፡

ወደ እስክንድርያ ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከርሳቸው ጋር ሊወስዱ ወድደው በግመል ላይ በጫኑት ጊዜ ግመሉ ከቦታው የማይነሣ ኾነ፤ ኹለተኛም ሌላ ግመል ቢጭኑ ርሱም የማይነሣ ኾነ፤ ስለዚኽ ዛሬ ድረስ የቅዱስ ሚናስ ሥዕል ሲሳል እነዚኽ ገመሎች አብረው ይሳላሉ፤ እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት ቦታ መኾኑን ዐውቀው የከበረ ሥጋውን በዚያው አኖሩት፤ ከዚያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለት ሰኔ 15 ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈጽሞ ብዙዎች ድንቆች ተደርገዋል።

በግብጽ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ቅዱስ ሚናስ ከጌታችን በተቀበለው ቃል ኪዳን በተማፀኑት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚደርስላቸው በእጅጉ ይወዱታል፤ በተለይ ከአቡነ ሺኖዳ በፊት ለነበሩት በቅድስና ሕይወታቸው ይታወቁ ለነበሩት ለአቡነ ቄርሎስ ቅዱስ ሚናስ ተገልጦላቸው እንደባረካቸው ይነገራል።


የቅዱስ ሚናስ በረከት ይደርብን!

አእላፍ መላእክት/ለ99ኙ ነገደ መላእክት

   


እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ (100): በክፍለ ነገድ አሥር (10) አድርጉዋቸዋል:: አቀማመጣቸውንም በ3 ሰማያትና በ10 ከተሞች (ዓለማት) አድርጉዋል::


+መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ "ኤረር: ራማና ኢዮር" ይባላሉ:: አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ:-

1.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል: አህን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው)
2.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ)
3.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ)
4.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል)
5.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል)

6.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል)
7.ስልጣናት (አለቃቸው ሱርያል)
8.መኩዋንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል)
9.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል)
10.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው::

+ከእነዚህም
 *አጋእዝት:
 *ኪሩቤል 
*ሱራፌልና 
*ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በ3ኛው ሰማይ) ነው::

 *አርባብ:
 *መናብርትና
 *ስልጣናት ቤታቸው ራማ (2ኛው ሰማይ) ነው::

 *መኩዋንንት:
 *ሊቃናትና 
*መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በ1ኛው) ሰማይ ነው::

+መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው:: አይራቡም: አይጠሙም: አይዋለዱም: አይሞቱም:: ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው:: ተግባራቸውም ዘወትር "ቅዱስ: ቅዱስ: ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው:: ምግባቸውም ይሔው ነው::

+ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም:: "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ: ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል:: በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም: ለመዓትም ይላካሉ::
ቅዱሳን መላእክተ ብርሃን: መንፈሳውያን: ሰባሕያን: መዘምራን: መተንብላን (አማላጆች) ተብለውም ይጠራሉና ያስቡን ዘንድ ልናስባቸው ይገባል::


የመላእክት ባሕርይ እንዴት ነው?

የመላእክት ባሕርይ ከሰው ጋር የሚያመሳስለውም የሚያለያየውም ነጥብ አለው፡፡ ከሰው በምን ይለያሉ ቢሉ መላእክት፡-
·        ረቂቃን ናቸው፡፡ ከነፋስ ነፍስ ትረቃለች፤ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ፤ ከመላእክት ደግሞ ሥላሴ ይረቃሉ፡፡
·        እንደ ሰው አይራቡም፤ አይጠሙም፡፡ ልብስ፣ መጠለያ አይፈልጉም፡፡ “እኔም ተገለጥኩላችኁ፤ ነገር ግን እይታን አያችኁ እንጂ ከእናንተ ጋር አልበላኹም፤ አልጠጣኹምም” /ጦቢት 12፡19/፡፡
·        የመላዕክት ምግባቸው የእግዚአብሔር ምስጋና መጠጣቸውም የመለኮት ፍቅር ነው፡፡
·        መላዕክት ፆታ የላቸውም /ማቴ.22፡30-31/፡፡ በመኾኑም አይጋቡም፤ አይዋለዱም፡፡
·        ስለ ነገ አይጨነቁም፡፡
·        መላዕክት ከዝንጋዔ የራቁ፣ ባለ አዕምሮ የኾኑ፣ ዕውቀት ያላቸው፣ ይዋኄንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዘለዓለም የማይነጥፍና የማያቋርጥ ይልቁንም ዘወትር እንደ ዥረት ውኃ የሚወርድ ምስጋና ያላቸው ናቸው /ሥነ ፍጥረት፣ በቀሲስ ስንታየኁና በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የተዘጋጀ፣ ገጽ 34/፡፡  
·        ምንም እንኳን ከሰው በፊት ቢፈጠሩም አያረጁም፡፡ ዘወትር ውቦች፣ ብርቱዎችና ውርዙዋን ናቸው፡፡
·        ኢ-መዋትያን ናቸው (አይሞቱም) /ሉቃ.20፡36/፡፡ ይኸውም ልክ እንደ እኛ ነፍስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ ነው፡፡  
·        እንደ ሰው አንድ ጊዜ ደግ ሌላ ጊዜ ክፉ በመሥራት አይዋልሉም፡፡
ከሰው ምን ያመሳስላቸዋል ስንል ደግሞ፡- ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ሕልውና ከአካል ጋር አላቸው፡፡ ዮሐንስ ዘደማስቆ የተባለ አባት ይኽን ሲያብራራው፡- “መላእክት ረቂቃን ናቸው የምንላቸው ከእኛ አንጻር ነው፡፡ ከማንም ጋር ከማይነጻተረው ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታዩ ግን ግዙፋን ናቸው፡፡ ፍጹም ረቂቅ እግዚአብሔር ብቻ ነውና” ብሏል፡፡
ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ውሱናን ናቸው፡፡ እንደ ሰው በቦታ የሚገቱ ባይኾኑም መጠን አላቸው፡፡ መጠናቸውና አርዐያቸውም የተለያየ ነው፡፡ ቁመታቸው ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መላዕክት አሉ፡፡ በክንፋቸው ብቻ አንድ አገር የሚያለብሱ መላዕክት አሉ፡፡ ራሳቸው ብቻ ተራራ የሚያክሉ መላዕክት አሉ፡፡ በዓይን የተቀረፁ የተሸለሙ ኹለንተናቸው ዓይን የኾነ መላዕክት አሉ፡፡ ስድስት ክንፍ ያላቸው መላዕክት አሉ፡፡ መብረቅ ለብሰው መብረቅ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ ነፋስ ለብሰው ነፋስ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ ብሩህ ደመና ጠምጥመው የሚኖሩ መላዕክት አሉ፡፡ እግራቸው ዓምደ እሳት የሚመስል መላዕክት አሉ፡፡ የእነዚኽን መላዕክት አርዓያቸውን መጠናቸውን ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቀው የለም /ኩፋ.2፡7-8/፡፡

ዐዋቂዎች ናቸው
ዕውቀታቸው ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ነው /2ኛ ጴጥ.2፡11/፡፡ ምንም ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ቢኾንም ግን ዕውቀታቸው መጠን አለው፡፡ ከእግዚአብሔርን በቀር ፍጹም ዕውቀት ያለው የለምና፡፡ እኛ ዕውቀታችን እንደ መላእክት የሚኾነው ከትንሣኤ ዘጕባኤ በኋላ ነው /1ኛ ቆሮ.13፡12/፡፡

 ነጻ ፈቃድ አላቸው
እንደ ሰው ባሕርያቸውን የሚገልጽ ስም አላቸው፡፡
 ሰው ከመበደሉ በፊት ልክ እንደ መላእክት ንጹሕ፣ ውብና ብርቱ ነበር፡፡ በፍጥረታት ላይ ሥልጣን ነበረው፡፡ ርሱ ሲበድል ግን ከሥልጣን የወረደ ሰው እንደ ድሮ የሚያከብረው እንደሌለ ኹሉ ፍጥረታቱ አዳምን አልታዘዝ አሉት፡፡ እንደዉም ተበረታቱበት፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውም ወደ ቀድሞ ክብራችን ወደ ልጅነት ወደ ቀድሞ ቦታችን ወደ ገነት ከዚያም በላይ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሊመልሰን ነው፡፡ በመኾኑም ሰው ምንም እንኳን በዚኽ ዓለም ሳለ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፍም በመጨረሻ መላእክትን ይመስላል፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱሳን መላእክት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ.1፡14 ላይ እንደገለጸው ታናሽ ወንድማቸውን ሰውን በማገልገል ላይ ያሉት፡፡

<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>

ቅድስት በርባራ

🌹 ቅድስት በርባራ ማናት? 🌹 ቃልኪዳኗስ? 🌹 ዐበይት በዓላቶቿስ መቼ ይታሰባሉ? 🫴 እኒህን ጥያቄዎች፦ በስሟ የምንማጸን፤ በስሟ ጽዋ የምንቃመስ፤ ዝክሯን የምናዘክርና በዓላቶቿን የምናከብር ቤተሰቦች ልናውቅ ይገባል። በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፨ ታኅሣሥ 8 በዓሏ የሚከበረው፣ ቃል ኪዳኗ ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው፣ የ15 ዓመቷ ሰማዕት የቅድስት በርባራ እና የቅድስት ዮልያና ድንቅ ታሪክና ገድል በአጭሩ፨ (ከገድለ ቅድስት በርባራ የተወሰደ) ❖ የተቀበለችው ቃል ኪዳን ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው በመላው ዓለም ከጥንት ጀምሮ የምትታወቀው ከ273-306 ዓ.ም የነበረችው ሰማዕቷ ቅድስት በርባራ ✨ በተለምዶ ቅድስት አርሴማ የምንላት ሥዕል የቅድስት በርበራ ሲሆን ለመለየትም በሥዕሏ ላይ Αγία Βαρβάρα (ቅድስት በርባራ) የሚለውን ጽሑፍ መመልከት ይቻላል። ✨ ቅድስት በርባራ (ባርባራ) ዘኒቆምድያ {Αγία Βαρβάρα, Great Martyr Barbara} ከ305-311 በነገሠው በከሓዲው መክስምያኖስ (emperor Maximian) ዘመነ መንግሥት መስፍን የነበረው የዲዮስቆሮስ ልጅ ናት። እናቷ በልጅነቷ ስለሞተች እና እጅግ ውብ ስለነበረች ሰው እንዳያያት ጣዖት አምላኪ የነበረ አባቷ ከከተማ ውጪ ለርሷም ለብቻዋ ሰገነት ያለው ማረፊያ ታላቅ ሕንፃ አሠርቶላት አንድ አረማዊ (ጣዖት አምላኪ) መምህር ብቻ ወደርሷ እንዲገባ አደረገ። ያሠራላት ሰገነት ከፍ ያለ ስለነበር አበባዎችን ይልቁኑ በምሽት የሚያበሩትን ከዋክብት የምሽቱ አስደናቂ ግርማ እየተመለከተች መደነቅ ጀመረች። በዚህ ጊዜ እነዚህ የአባቷ ጣዖታት አስደናቂ ዓለማትን እንደማይፈጥሩ መረዳት ጀመረች። በቤቷ ውስጥም ካሉ ሴት አገልጋዮች አንዴ ይህንን ጥያቄዋን አይታ የክርስቲያን መምህር ጠቆመቻት። ይህንንም መምህር አርጋኖስ በደብዳቤ አድርጋ የነፍሷን መሻት ነገረችውና ደቀ መዝሙሩን በድብቅ ልኮ ስለ ምስጢረ ሥላሴ፣ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን ተማረች። እውነተኛውን የድኅነት መንገድ በመረዳቷ ከእስክንድርያ ወደ ሄሊዎፓሊስ መጥቶ በነበረ ካህን በድብቅ በግቢዋ ባለ መዋኛ ገንዳ ተጠመቀች።
በይበልጥም የሰማዕታትን ታሪክ በተመስጦ ታነብ ጀመር። በድንግልና ለመኖርም ከበርቴ ባሎችን እምቢ ብላ መለሰች። በድብቅም በጸሎትና በጾም ትተጋ ጀመረች። አባቷም ወደዚኽ ሕንጻ በገባ ጊዜ ልጁ ያሠራችውን አይቶ ዐናጺዎችን ሲጠይቃቸው፤ ይኽነን እንዲሠሩ ያዘዘቻቸው ልጁ መኾኗን ነገሩት። እርሱም “ለምን እንደዚኽ አደረግሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ወትቤሎ አእምር ወለቡ ኦ አቡየ እስመ በሥሉስ ቅዱስ ይትፌጸም ኲሉ ግብር በእንተዝ አግበርኩ ሣልሲተ መስኮተ፤ ወዘንተኒ መስቀለ በአምሳለ ስቅለቱ ለመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይላል ርሷም “አባቴ ሆይ አስተውል፤ ልዩ ሦስት በኾነ በሥላሴ ስም ሥራ ኹሉ ይፈጸማልና ስለዚኽ ሦስተኛ መስኮት አሠራኊ፤ ይኽም መስቀል ዓለሙ ኹሉ በርሱ በዳነበት በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትኽ ተመልሰኽ የፈጠረኽን አምላክ አምልከው” በማለት ተናገረችው፡፡ 🌿 የቅድስት በርባራ እና የቅድስት ዮልያና ትውውቅ 🌿 አባቷም ከርሷ ይኽነን በሰማ ጊዜ በንዴት ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ። ያን ጊዜ ሸሽታ በተአምር ለሁለት በተከፈለች ዐለት ውስጥ ገብታ ለጊዜው ብትሸሸግም በኋላ ግን ወደ አባቷ ተመለሰች። እርሱም እንድትሠቃይ ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት፤ ርሱም እየገረፈ በጊዜው አሉ በተባሉ በታላላቅ ሥቃይን ቢያሠቃያትም የባሕርይ አምላክ ክርስቶስን ግን አልካደችም። ከዚያም ብቻዋን ወደ ወህኒ ተጣለች፤ በዚያም ኾና “ጌታዬ አምላኬ ሆይ አትተወኝ” ብላ ጸለየች፤ በእኩለ ሌሊትም የእስር ቤቱን ደማቅ ብርሃን መላው፤ “ከአንቺ ጋር ነኝና አትፍሪ” የሚለውን የአምላክን ድምፅ ሰማች፤ ከዚያም ጌታችን ቊስሎቿን ኹሉ ፈወሰላት፡፡ ✨ ቅድስት በርባራ ከአባቷ ስትሸሽ አንዲት ዐለት ተከፍታ ብትደብቃት በዛ አካባቢ ያለ አንድ ክፉ እረኛ ለአባቷ ተናግሮ አስያዛት። በዚህም ቅድስቷ አዝና ብትረግመው ከነከብቶቹ ወደ ትልነት ተቀይሯል። ✨ በነጋታው ቅድስት በርባራን በማርቲያኑስ ፊት አቆሟት። ኹሉም ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደዳነችና ፊቷም እንደ ፀሓይ ጨረር ሲያንጸባርቅ ተመለከቱ። መኰንኑም “አማልክቶቻችን ስለፈወሱሽ የምስጋና መሥዋዕትን ሠዊ” አላት፤ ቅድስት በርባራም ለአገረ ገዢው “በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው የዳንኩት” አለችው፡፡ ✨ ቅድስት በርባራ ከአባቷ ተከፍታ የደበቀቻት ዐለት በአሁን ጊዜ (የውስጥ ገጽታ) Village of Aboud, Palestine ✨ ✨ ቅድስት በርባራን ከአባቷ ስትሸሽ ተከፍታ የደበቀቻት ዐለት በአሁን ጊዜ (የውጪ ገጽታ ከታች ካለው ምስል ይመልከቱ!) ✨
በዚያም ዮልያና ነበረችና ቅድስት በርባራን ሲያሰቃይዋት አይታ ከርሷ ጋር በክርስቶስ ስም መከራን ለመቀበል በመወሰን አብራት መከራ መቀበል ጀመረች። ሁለቱም ሰማዕታትን በምስማር ሰውነታቸውን እየወጉ ያሰቃይዋቸው ነበር። ለመዘባበት ዕርቃናቸውን በአደባባይ ሊወስዷቸው ቢሞክሩም በቅድስት በርባራ ጸሎት ጌታ መልአኩን ልኮ በአስደናቂ መጎናጸፊያ ሰውነታቸውን በብርሃን ልብስ ጋርዶታል። በመጨረሻም ጨካኙ መኰንን ብዙ ዐይነት ሥቃይ ቢደርስባቸው እነዚኽ ቅዱሳት አንስት በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንደማይለውጡ ባየ ጊዜ አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘ። 🌿 ሰማዕትነት እና ቃልኪዳን 🌿 ከወታደሮቹ መኻከል አንዱ አንገታቸው ለመቊረጥ ሰይፉን መዘዘ። በአባቷ ወደ ተዘጋጀው ወደ መግደያው ስፍራ ይዟቸው ሔደ። ያን ጊዜ ቅድስት በርባራ እንዲኽ ብላ ጸለየች “ዘላለማዊ እግዚአብሔር ሆይ ከእኔ ሞት በኋላ እኔንና መከራዬን ለሚያስቡ ኹሉ ሥጦታኽን ስጣቸው፤ ድንገተኛ ሕመምና ብርቱ (አስጨናቂ) ሞትን በእነርሱ ላይ ፈጽሞ አታምጣባቸው” አለች፡፡ ከዚያም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ መሻቷን ኹሉ እንደሚፈጽምላት ቃል ኪዳን ሲገባላት በሰጣት ቃል ኪዳን የሚታመኑ ኹሉ ድንገተኛ ሞት እንደማያገኛቸው ቃል ኪዳን ገባላት። በመጨረሻም አባቷ የርሷንና የባልንጀራዋ የዮልያና አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘና በ15 ዓመቷ ታኅሣሥ 8፥ በ306 ዓ.ም. አንገታቸው ተቈርጦ የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጁ፤ ቅድስት ዮልያናንም በኹለት ጡቶቿ በኩላብ ሰቅለው ሰይፈዋታል፡፡ በዚያን ጊዜ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የኾነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው። ከዚኽ የተነሣ በዓለም ባለው ሥዕሏ ላይ የመብረቅ ብልጭታ ይሣላል፡፡ ቅድስት በርባራም በዚህ ምክንያት በአማላጅነቷ ከጥንት ጀምሮ ባሉት ክርስቲያኖች ከመብረቅ አደጋና ከእሳት የምትጠብቅ እንደሆነች ይነገራል።
ያም በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በመስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ኹሉ ከርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን ኾነ። ከዚኽም በኋላ የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጪ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሯቸው። ይኽ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለ ቤተ ክርስቲያን ተቀመጠ፡፡ ✨ ይኽችም ሰማዕተ ክርስቶስ ቅድስት በርባራ፥ ምእመናን ከተቀደሱ ምሥጢራት ለመውሰድ ሳይችሉ ቀርተው እንዳይሞቱ በስሟ የሚማጸኑባት ናት። ይኽችም ሰማዕተ ክርስቶስ ቅድስት በርባራ፥ ምእመናን ከተቀደሱ ምሥጢራት ለመውሰድ ሳይችሉ ቀርተው እንዳይሞቱ በስሟ የሚማጸኑባት ናት። በአንድ ወቅት አንድ ኢስታንሲ ላወስ የተባለ ቅዱስ መነኵሴ የሞቱ ጊዜ በተቃረበ ሰዓት ቅዱስ ቍርባን የሚያቀብለው አጣ። በቅድስት በርባራ ስምም አምላኩን ተማጸነ። በዚህም ጊዜ ቅድስት በርባራ ልመናውን ሰምታ፥ ከኹለት ካህናት ጋር ተገለጸችለት። ከኹለቱም አንደኛው ካህን ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን አቀበለው። 📌 ከመድኃኔዓለም የተሰጣት ቃልኪዳን፦ ● ስሟን የሚጠራውን፣ ለስሟ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን፣ መታሰቢያ የሚያደርገውን፣ ● በስሟ በታነፀው ቤተ ክርስቲያን ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ ልዩ ልዩ የቤተ መቅደስ መገልገያዎችን የሚያመጣውን፣ ● ልጁን በስሟ የሰየመውን፣ ለመድኃኔዓለም ስትል የተቀበለችውን መከራ የሚያስብ በስሟ ተማጽኖ ቢለምን እስከ 10 ትውልድ ድረስ ምሕረትን ያገኛል፤ ● በስሟ ለታመነ ከድንገተኛ አደጋ፦ ከመብረቅ፣ ከእሳት፣ ከዐውሎ ንፋስ፣ ከፍንዳታዎች ይድናል። 🌿 ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት እና ሰማዕቷ 🌿 ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ቅድስት በርባራን አመስግነው በቃኝ አይሉም ነበር፤ ለምሳሌ ያህል ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ቅዱስ አርከ ሥሉስ እንዴት እንዳመሰገኗት እንይ። 🌹“ሰላም ለበርባራ ወዮልያና በፍኖተ ስምዕ እለ ቆማ፥ እለ ተጋደላ ከመ ሐራ፥ ● ሙሽራቸው ክርስቶስን እስኪያገኙ ድረስ ድንግልናቸውን የጠበቁ፤ የክርስቶስ መከራ መስቀሉን የተሸከሙ፤ እንደ ጭፍሮች የተጋደሉ፤ ሩጫቸውንም የፈጸሙ፤ በምስክርነት ጎዳና የቆሙ ለሆኑ ለበርባራና ለዮልያና ሰላምታ ይገባል በማለት አወድሷቸዋል፡፡ [ተአምኆ ቅዱሳን ንባቡና ትርጓሜ ገጽ 401] 🇨🇬 አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአርጋኖን (ዘእሑድ 9፥4-6) ድርሰቱም ላይ እመቤታችንን "የአርሴማ የበርባራ...የዮልያናን በረከት እንዲያርፍብኝ ለምኚልኝ" ይላታል። 🌹“ሰላም ለበርባራ እንተ አግሀደት ሃይማኖታ፥ ወሰላም ካዕበ ለዮልያና ካልዕታ እንተ ሰቀልዋ በክልኤ አጥባታ”🌹 ዳግመኛም በሁለት ጡቶቿ የሰቀሏት የርሷ ሁለተኛ ለምትሆን ለዮልያናም ሰላምታ ይገባል በማለት የተቀበሉትን ጽኑ መከራ ጽፏል፡፡ በክልኤ ዕደው ዘሰረቁ መጽሐፈ ገድላ፥ ✨ ቅድስት በርባራ እና ቅድስት ዮልያና ከእመቤታችን ጋር አባ ጊዮርጊስን ለገፉ አንድ መምህር እንደተገለጡ የአባ ጊዮርጊስ ገድል በተአምሩ ይናገራል። ✨ በእጅጉ የሚገርመው ከጥንት ዠምሮ በየክፍላተ ዘመናቱ እስከ ዛሬ ድረስ በበርካታ የዓለም ክፍሎች በቅድስት በርባራ ከሚፈነዱ የጦር መሣሪያዎች፤ ከመብረቅ አደጋና ከድንገተኛ ሞት በቃል ኪዳኗ እንደምትጠብቅ ሲታመን፤ በጣሊያን የባሕር ኀይላችን ጠባቂ (the patron of the Italian Navy.) ይሏታል። በቃል ኪዷና በእጅጉ ከመታመን የተነሣ በጊዜያችን ያሉ በርካቶች ኀያላን ሀገራት ብሪታኒያ (Royal Artillery, RAF Armoures, Royal Engineers) በካናዳ (Explosive Ordance Technicaians) በአውስራሊያ (RNZAF Armourers) በኒውዝላንድ፤ በስፔን፣ በአሜሪካ፣ በግሪክ የቅድስት በርባራን በዓል በዐየር ኀይላቸው፣ በጦር ካምፓቸው፣ በባሕር ኀይላቸው እንደሚያስቡ ጥናቶች በግልጽ ያሳያሉ።
ቅድስት በርባራ፥ በአደገኛ ሥራ ላይ ያሉ እና ከጦር መሣሪያ ጋር የሚሠሩ ሰዎች በድንገተኛ አደጋ እንዳይሞቱ በበራቸው፣ በምሽጋቸው፣ በመሥሪያ ቦታቸው፣ በጦር አርማቸው ላይ ያስቀምጧታል፤ ይሥሏታል። ሙሉ ገድሏን በpdf ለማግኘት👇 https://t.me/Ewnet1Nat/12037 ተወዳጆች ሆይ! ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ብቻ የምትሰሙ አትሁኑ፡፡ እነርሱን ለመምሰልም ተጣጣሩ እንጂ፡፡ ለጊዜው ብቻ የምታደንቋቸው አትሁኑ፡፡ ወደ ቤታችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ ልቡናችሁ ውሳጤም ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ፡፡ ዘወትር አስቧቸው፡፡ በልቡናችሁ ጓዳ እንዲገቡ አድርጓቸው፡፡ እናንተን ትተው ይሔዱ ዘንድ አትፍቀዱላቸው፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደሆነ ዘወትር እያያችኋቸው ትበረታላችሁ፡፡ በእምነት ትጸናላችሁ፡፡ የለበሱትን የጽድቅ ጥሩር፣ የያዙትን ምግባረ ወንጌል፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ እየተመለከታችሁ ትበረታላችሁ፡፡” የሰማዕታቱ በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደር! አሜን!

የእግዚአብሄር ልጅ ነው ፤ አምላክም ነው!

ሐዋርያትን የመሰለ የተመሰገነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴወስ ስለ እግዚአብሄር ቃል ሰው መሆን ነገሩን ከኒቅያ ማህበር 318 ሊቃውንት ጋር አስተባብሮ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ አምላክ ነው ፤ በመለኮት የእግዚአብሄር ልጅ በሥጋ የአዳም ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ የአዳም ልጅ ስለሆነም ለወልድ ዋህድ ለአንዱ የምንሰግድለት ለአንዱ ደግሞ የማንሰግድለት ሁለት አካል ሁለት ባህርይ አለው የምንል አይደለንም፡፡ ሰው የሆነ የእግዚአብሄር አካሉ ባህርዩ አንድ ነው እንጂ ፤ ከስጋው ሳንለይ አንድ አድርገን አንዲት ስግደትን እንሰግድለታለን እንጂ፡፡ ሁለት ነው ፤ አንዱ ከእግዚአብሄር የተገኘ የባህርይ አምላክ ነው ፡ ለእርሱ እንሰግዳለን ፤ ሁለተኛውም ከማርያም የተገኘ ሰው ነው ፡ ለእርሱ አንሰግድም አንልም፡፡ እርሱ ከሰው ቢወለድም በፀጋ የእግዚአብሄር ልጅ አይደለምና ፤ አስቀድሜ እንደተናገርኩ ከእግዚአብሄር የተገኘ እግዚአብሄር ነው እንጂ፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ነው ፡ ዳግመኛም በኅላ ዘመን በሥጋ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ ያው እርሱ ነው ፡ ሌላ አይደለም፡፡ ዮሐ 1 ፡ 1-18 ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የእግዚአብሄር የባህርይ ልጅ ነው ፤ እርሱም የባህርይ አምላክ ነው፡፡ መለኮት ቢያድርበት በፀጋ የከበረ አይደለም ፤ ስጋን በመንሳት ሰው የሆነ እርሱ ብቻ ነው ፤ በመለኮት
፤ እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ብቻ ነው፡፡ የእኛን መከራ ተቀበለ ፤ በመለኮቱ መከራ ሳይኖርበት ክርስቶስ ስለእኛ በሥጋ መከራ ተቀበለ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዳግመኛም ስለእኛ ስለሁላችን ቤዛ አድርጎ ለሕማም ለሞት ሰጠው እንጂ እግዚአብሄር ላንዱ ልጁስ እንኳን አላዘነም ብሎ እንደተናገረ፡፡ 1ጴጥ 3፡18፣19 ፤ ሮሜ 8 ፡ 32 እንደቀድሞው መታመም መለወጥ የሌለበት ሁኖ ኖረ፡፡ በነቢይ አድሮ የማይለወጥ አምላክ እኔ ነኝ ብሎ እንደተናገረ ፡ በመለኮቱ መለወጥ የለበትም፡፡ ሚል 3፡6 ሃጢአታችንን ስለማስተስረይ ለእኛ የሚገባ ሞትን ሞተ ፤ ቤዛችን በሚሆን ሞቱ ሞትን ያጠፋው ዘንድ ሞተ ፤ ሞት በመሽነፍ ባህር ተሰጠመ ፤ ሞት ፅናትህ የት አለ?መቃብርስ ማሽነፍህ የት አለ? ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረ፡፡ ኢሳ 25፡8 ፤ ሆሴ 13፡14 ፤ 1ቆሮ 15፡54 እንደተፃፈ ሃጢአታችንን ለማስተስረይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተ ፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት ቀድሞ እንደነበረ ለዘለዓለሙ ይኖራል ፤ በሞትም አይያዝም ፡ የማይታመም የእግዚአብሄር አብ ሃይሉ ነውና፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረ ሞት ሊይዘው አልቻለምና ፡ ወደ ሰማይ አረገ ፡ በአብ ዕሪና ተቀመጠ ፡ ይኅውም ዕርገት ነቢር ቃል ከአዳም ነስቶ በተዋሃደው ሥጋ የፈፀመው ነው፡፡ ራእ ዮሃ 1፡18 ፤ ግብ ሐዋ 2፡24 ፤ 1ጴጥ 3፡22 የእግዚአብሄርን ቃል ሲያመለክት ጌታ(አብ) ጌታየን(ወልድ) በቀኜ ተቀመጥ አለው ብሎ ነቢዩ ዳዊት በመፅሃፉ እንደተናገረ፡፡ መዝ 16 ፡(15) 7-11 ፤ ግብ ሐዋ2፡25 -28 ፤ ማቴ 22፡41 ፤ ቃል በመለኮቱ አይወሰንምና እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሰማይን ምድርን ይወስናል እንጂ ከቀዳማዊ አብ የተገኘ እርሱ ከዘመን አስቀድመው ከነበሩ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ ቀዳማዊ ነው፡፡መዝ 95(94)1-7 ፤ ኢሳ 26፡1 ፤ ዮሃ 1፡1-4 ክርስቶስ የእግዚአብሄር ኅይሉ ነው ፤ የእግዚአብሄር ጥበቡ ነው ብሎ ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተናገረ የማይመረመር የእግዚአብሄር አብ ኅይሉ ነውና፡፡1ቆሮ 1-24 በሙታን በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ይህ አንድ አምላክ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የእግዚአብሄር ልጅ ይመጣል ፡ እመጣለሁ ብሎ እንደተናገረ፤ በስውር የተሰራውን መርምሮ የሚፈርድ የልቡናን ሃሳብ የሚገልጥ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ይመጣል ፤ ለሁሉም እንደስራው ይከፍለዋል ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረ፡፡ማቴ 25፡1-46 ፤ 1ቆሮ 4-5 እግዚአብሄር ካፃፋቸው መፃሕፍት ከተገኘ ከዚህ ትምህርት ሌላ የሚያስተምረውን የእግዚአብሄር ልጅ ፡ ከማርያም ከተወለደው ልዩ ነው የሚለውን አንዱ አካል የእግዚአብሄር ልጅ ፡ አንዱ ከማርያም የተወለደ በፀጋ የከበረ ዕሩቅ ብእሲ ነው ብሎ ሁለት እስከማለት ደርሶ እንደእኛ በፀጋ የከበረ የፀጋ ልጅ ነው የሚለውን ፤ ጌታችን የነሳው ስጋ ከሰማይ እንደተገኘ ፡ ከድንግል ማርያምም እንዳልተገኘ አድርጎ የሚናገረውን ወይንም መለኮት ስጋ ወደመሆን ተለወጠ ፡ ወይም ከእርሱ ጋር ተቀላቀለ ፤ ወይም መለኮት በባህርይው ታመመ የሚለውን ወይም መለኮት ያልተዋሃደው የዕሩቅ ብእሲ ሥጋ ነውና ጌታችን ለተዋሃደው ስጋ አልሰግድለትም የሚለውን የጌታችን ሥጋ አምላክ ነውና እሰግለታለሁ የማይለውን እንዲህ እንዲህ የሚሉትን የእግዚአብሄር ልጅ የሾመው ሐዋርያ እኛ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሁሉ የተወገዘ ፡ የተለየ ይሁን ያለውን ቃል ይዛ ቅድስት ቤተክርስቲያን ታወግዛቸዋለች ፡ ትለያቸዋለች፡፡ ገላ 1፡6-10 መናፍቃንም ሰው ሆነ ስለማለት ፋንታም ራሳቸውን ለመጉዳት ልብወለድ ነገርን ፈጥረው “እግዚአብሄር በሰው አደረ” አሉ ፤ መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ተዋሃዱ ስለማለት ፋንታ ሰው ሰራሽ ነገርን ፈጥረው ተናገሩ ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አንድ ነው ስለማለት ፋንታ ሁለት ባህርይ ፡ ሁለት አካል ፡ ሁለት ገፅ ብለው አመኑ ፤ በሶስቱ አካላት ስለማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩበት በማይገባ ሥራ አራት ብለው አመኑ፡፡ ይህም የማይገባ የማይጠቅም ክህደት ነው ፤ ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር አቆራኝተዋልና ፤ ተገዥንም ከገዥ ጋር አንድ አድርገዋልና ፤ ካልተፈጠሩ አካላት ጋር ልዩ አራተኛ አካል አለ ብለዋልና፡፡በክህደታቸው በሶስቱ አካላት ላይ ከመላእክት በኅላ የተፈጠረ ሌላ አንድ አካል ይጨምራሉና ሶስት ስለማለት ፋንታም አራት ብለው ይሰግዳሉ፡፡ 1ጢሞ 2፡16-19 ፤ 2ጴጥ 2፡1-13 ፤ እነዚህ የተረገሙ ናቸው ፤ ትምህርታችውንም የያዘ የተረገመ ነው፡፡ ማቴ 25፡41 ፤ 2 ጴጥ 2፡14-22 ከሃድያን ጳውሎስ ሳምሳጢና መርቅያን እንደተረጎሙላቸው መጠን ይልቁንም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሰው ሁሉ ለስላሴ ይሰግዳል ፡ ያገለግላል ፡ ይገዛላቸዋል ይላሉ እንጂ ለእርሱ አይሰግዱም ፤ ሐዋርያት ያስተማሯቸው አምላክ አዝዞ ያፃፋቸው መፃህፍት ያልተናገሩትን የማይገባ ነገርንም ይናገራሉ አሉ፡፡ ከመምህራን ተለይተው በምክር አንድ ሆነው ሥጋን ሳይዋሃድ ሰው ከመሆን አስቀድሞ በጌትነት በምልአት የነበረ ፤ ሰው በሆነ ጊዜም በጌትነት በምልአት ያለ ሲሆን በሁሉ ለሁሉ ገዥ ይሆን ዘንድ ሁሉን ባስገዛለት ጊዜ ሁሉን እንዲገዛለት ላደረገ ለአብ ወልድም ይገዛል እያሉ እንደ ወደዱ ይተረጉሟቸዋል፡፡ ያደረበት ሰው ግን ከፍጡራን ሁሉ እንደአንዱ ነው ፡ ለእግዚአብሄር ይሰግዳል ፡ ይገዛል ፡ አሉ ፤ እንዲህ ባለ ድንቁርና እንደተያዙ ዕወቁ ፤ ራሳቸው አዋቆች እንደሆኑ ያስባሉ ፡ የወደቁበትን ይህን የአእምሮ ማጣትና የስንፍና ብዛትን እዩ ፡ በመፃህፍት የማይገኘውን ከልቡናቸው አንቅተው እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ ኢሳ 5፡19 ፤ ዮሃ 8፡44(45) ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር የባህርይ ልጅ ሲሆን ሰው ይባላል ፤ ዳግመኛም የአዳም ልጅ ይባላል ፤ ሰማያዊ ሲሆን በፈቃዱ ምድራዊ ሆነ ፤ በመለኮቱ መከራ መቀበል ሳይኖርበት ሰው በመሆኑ መከራ ተቀበለ ፤ ፈፅሞ አንዱ በአንዱ ያደረ ነው አይባልምና ፡ ለአንዱ ለእግዚአብሄር ልጅ ሁለት አካል ሁለት ገፅ ሁለት ባህርይ የለውም፡፡ ዮሃ 3፡12(13) ፤ ዮሃ 5፡27 ፤ ሮሜ 5፡8-11 ፤ 1ቆሮ 5 ፡ 14 እኛ ኢየሱስ ክርስቶስን የማይታመም ሰማያዊ አምላክ እንደሆነ እናውቀዋለን ፡ ዳግመኛም በሥጋ ከዳዊት ባህርይ የተገኘ የሚታመም ምድራዊ ሰው ኢንደሆነ እናውቀዋለን ፤ እንደምን ባለ ስራ ፡ እንደምን ባለ ነገር የሚታመም የማይታመም ሆነ? ብለን አንጠራጠር ፡ አንድ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አምላክ ነው ፡ ሰውም ነው፡፡ የመለኮትና የትስብእት ተዋህዶ እንደምን እንደሆነ ምሳሌ በመሻት አንመራመር ፡ አንሳት ፡ አንጠራጠር ፡ ተዘጋጅቶልን ካለ ከመንግስተ ሰማያት ክብር እንዳንለይ፡፡ ከሁሉ የሚበልጥ በዚህ ሃይማኖት በልቡናህ ታምን ዘንድ ይገባል፡፡ ዳግመኛም በዚህ ሃይማኖት ትፀና ዘንድ በአርያም ያለ እግዚአብሄርን ለምነው ፡ ከስጋዊ ከደማዊ ፡ ከምድራዊ ፈላስፋ ይህን ልትማር ለአንተ አይገባም ፡ በአርያም ካለ ከእግዚአብሄር ዘንድ ነው እንጂ፡፡ እርሱ ራሱ ጌታችን ሰማያዊ አባቴ ነው እንጂ ይህን ስጋዊ ደማዊ መምህር የገለጠልህ አይደለምና ነተ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ብፁህ ነህ ፡ አንተ መሰረት ነህ ፡ በአንተ መሰረትነት ቤተክርስቲያንን አንፃታለሁ ፡ የሲኦል አበጋዞች አጋንነትም ድል አይነሷትም ብሎ እንዲህ ተናግሯልና፡፡ ምንጭ ሃይማኖተ አበው ዘ አትናቴወስ የእግዚአብሄር ቸርነት ፡ የእመቤታችን አማላጅነት ፡ የአባታችን የቅዱስ አትናቴወስ በረከትና ረድኤት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

አርባዕቱ እንስሳ

የኃያሉ እግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ የአርባዕቱ እንስሳ በዓል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በኅዳር ወር ስምንት ቀን ይከበራል፡፡ እነዚህም መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው፤ ስለ እርሳቸውም ወንጌልን የጻፈ ዮሐንስ እንዲህ ሲል እንደመሰከረ ‹‹በዚያ ዙፋን ፊት በረድ የሚመስል ባሕር አለ፤ በዙፋኑም ዙሪያ አራት እንስሶች አሉ፤ በፊትም በኋላም ዓይንን የተመሉ ናቸው። የፊተኛው አንበሳ ይመስላል፤ ሁለተኛውም ላም ይመስላል፤ ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል፤ አራተኛውም የሚበር አሞራ ይመስላል። የእነዚህም የአራቱ እንሰሶች እያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው፤ ሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፤ የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽኑዕ ክቡር ልዩ ነው፤ እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም።›› ሁለተኛውም ስለ እርሳቸው ኢሳይያስ እንዲህ አለ፤ ‹‹ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኦዝያን በሞተ ጊዜ አሸናፊ እግዚአብሔርን ሰፊ በሆነና ከፍ ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ብርሃኑም ቤቱን መልቶ ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው አየሁት። የአንዱም የአንዱም ክንፋቸው ስድስት ነው፤ በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን በሁለቱ ክንፋቸው እግሮቻቸውን ይሸፍናሉ፤ በሁለቱ ክንፎቻቸው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበራሉ፤ አንዱም አንዱም ከአንዱ ጋራ ‹‹ፍጹም አሸናፊ የሆንክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በምድርና በሰማይ የመላ ነው›› እያሉ ያመሰግናሉ። ነቢይ ዳዊትም ‹‹በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ›› አለ፤ ‹‹ሁለተኛም በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ እርሱ ምድርን አናወጻት›› አለ። ሕዝቅኤልም እንዲህ አለ፤ ‹‹ከወደ ሰሜን እነሆ ጥቅል ነፋስ ሲመጣ አየሁ፤ ታላቅ ደመና አለ፤ በዙሪያውም ብርሃን አለ፤ ከእርሱም እሳት ቦግ ብሎ ይወጣል። በደመናውም መካከል ባለ በእሳቱ ውስጥ እንደ አራት ራስ አሞራ መልክ የሚመስል አለ፤ በመካከሉም እንደ አራቱ ኪሩቤል መልክ ያለ አለ፤ መልካቸውም እንዲህ ነው፤ በውስጣቸው የሰው መልክ አላቸው፤ የአንዱም የአንዱ ፊቱ አራት ነው፤ ክንፉም አራት ነው። እግራቸውም የቀና ነው፤ ከእግራቸውም ክንፍ አላቸው ሰኮናቸው ግን እንደ ላም ሰኮና ነው፤ ከእርሱም እሳት ቦግ ይላል፤ እንደጋለ ብረት ፍንጣሪም ይበራል።›› ወንጌላዊ ዮሐንስም ዳግመኛ እንዲህ አለ፤ ‹‹በዚያው ዙፋን ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ የእንስሶቹንም የእነዚያ አለቆችንም ቃል ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም እልፍ አለቆች ያሉአቸው ብዙ የብዙ ብዙ ነው። ለዚያ ለተገደለው በግ ኃይልን፣ ባለጸግነትን፣ ጥበብን፣ ጽናትን፣ መንግሥትን፣ ክብርን፣ ጌትነትን፣ ምስጋናን ገንዘብ ሊያደርግ ይገባዋል ብለው በታላቅ ቃል ተናገሩ። በሰማይና በምድር ከምድር በታች በባሕር ውስጥ በእነዚያም ውስጥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ጌትነት ክብር ኃይል በረከት በዙፋኑ ለተቀመጠው ለእርሱ ለበጉም ለዘላለሙ ይገባዋል አሉ፤ በእውነት ይገባዋል፤ እነዚህም አራቱ እንስሶች አሜን ይላሉ፤ እነዚያም አለቆች ይሰግዳሉ።›› ስለ ልዕልናቸውና ስለ ክብራቸው ለእነዚህ አርባዕቱ እንሰሳ ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል፤ መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው። ዳግመኛም እንዲህ ተባለ፤ ‹‹ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፤ ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል፤ ገጽ ላሕም ስለ እንስሳ ይለምናል፤ ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል፤ ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና።›› ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነፁ በዚችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ፤ እነርሱ ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና። እግዚአብሔር አምላካችን በቅዱሳን አርባዕቱ እንስሳ አማላጅነት ይማረን፤ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን። ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር

ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ

ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ፡- ምግባር ሃይማኖታቸውና እጅግ ጽኑ የሆነው ተጋድሎአቸው ‹‹አባ›› ተብለው እንዲጠሩ አደረጋቸው እንጂ ገና የ12 ዓመት ሕፃን ናቸው፡፡ በሰማዕትነት ያረፉት በተአምራት ካሳመኗቸው ከ190 ሺህ ማኅበርተኞቻቸው ጋር ነው፡፡ ከደቡባዊ ግብፅ ከንሂሳ ገዳም የተገኙ ታላቅ ሰማዕት ናቸው፡፡ በተወለዱ በ5ኛ ቀናቸው መልአክ ሲያነጋግራቸው ወላጆቻቸው አይተው በአንክሮ እያዩ አሳደጓቸው፡፡ የነበሩበት ዘመን የክርስቲያኖች ደም እንደ ውሃ በሚፈስበት በከሃዲው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ስለነበረ አባ ኖብ ወደ ሰማዕትነቱ በፈቃዳቸው ሔደው በከሃዲው ንጉሥ ፊት ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ሔዱ፡፡ ሲሔዱም አንድ ጻድቅ ‹‹አባ አትሒዱ›› ቢላቸው ‹‹የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ቁልፍ ልቀበል ነው የምሔደው›› ብለውት ሔዱና በከሃዲዎቹ ነገሥታት ፊት የአምላካቸውን ክብር መሰከሩ፡፡ የታሠሩ ክርስቲያኖችን በክርስቶስ ማመናቸውን እስከመጨረሻው አጽንተው የተዘጋጀላቸውን የጽድቅ አክሊል እንዲወርሱ ይመክሯቸው ነበር፡፡ አባ ኖብም የወላጆቻቸውን ሀብት ለድኆች መጽውተው ወደ ሰማዕትነቱ ሲሔዱ መኰንኑ አገኛቸውና ‹‹ክርስቶስን ክደህ ለጣዖቶቻችን ስገድ›› ቢላቸው ከንቱነቱን ነግረው አስተማሩት፡፡ በብዙ አሰቃቂ መከራዎችም በእጅጉ አሰቃያቸው፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ፈወሳቸውና ወደፊት የሚደርስባቸውን ነገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ አትሪብ በመርከብ ይዟቸው ሲሔድ በመርከቡ ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ በመስቀል ሥጋቸው እስኪቆራረስ ድረስ በብረት በትር አስገረፋቸው፡፡ መኰንኑም እርሳቸውን እያስገረፈ እርሱ ተቀምጦ ሊበላና ሊጠጣ በፈለገ ጊዜ እመገባለሁ ቢል ምግቡ ድንጋይ ሆነበት፡፡ የአሽከሮቹም ዐይን ታወረ፡፡ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከስቅላታቸው አውርዶ ቍስላቸውንም ፈውሶ ደማቸውን ጠረገላቸው፡፡ አባ ኖብም ጸልየው የታወሩትን ሰዎች የዐይናቸውን ብርሃን መልሰውላቸው አስተምረው ወደ ሃይማኖትም መለሷቸው፡፡ እነርሱም መስክረው ሰማዕት ሆነው ተሰይፈዋል፡፡ ወደ አትሪብም ከደረሱ በኋላ አባ ኖብን ግን ስቃዩ ይጥናባቸው ብለው በብረት ችንካሮች ቸንክረዋቸው በብረት አልጋ ላይ አድርገው እሳት አነደዱባቸው፣ በመጋዝም ሰነጠቋቸው፣ ሰውነታቸውን ቆራርጠው ጣሉት፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ አዳናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወሰዷቸውና ብዙ አሰቃዩአቸው፡፡ ለመርዛማ እባቦች ቢሰጧቸውም ምንም አልነኳቸውም ይልቁንም አንዱ እባብ ሔዶ በመኰንኑ አንገት ላይ ተጠምጥሞ ነድፎ ለሞት አደረሰው፡፡ ሟርተኞቹ እንዳላዳኑት ካወቀ በኋላ አባታችን እባቡን ከአንገቱ ላይ እንዲወርድ አድርገው ፈወሱት፡፡ መኰንኑም ዳግመኛ በእሳት እንዲያቃጥሏቸው ቢያዝም እሳቱ እሳቸውን ማቃጠልን እምቢ አለ፡፡ መኰንኑ ማሰቃየቱ በሰላቸው ጊዜ አንገታቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ አባ ኖብ ስለ ክርስቶስ እየመሰከሩ ጽኑ መከራን እየተቀበሉ ለብዙ ዓመታት ከተሰቃዩና ከጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ሐምሌ 24 ቀን አንገታቸውን ተሰይፈው ሰማዕትነታቸውን ፈጽመዋል፡፡ 190 ሺህ ሰማንያ አራት የአባ ኖብ ማኅበርተኞችም እንዲሁ በሐምሌ 24 ተሰይፈው ሰማዕት ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ሺዎቹ በዛሬዋ ዕለት በዓመታዊ በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡ የሰማዕቱ የአባ ኖብ ቤተ ክርስቲያናቸው በአገራችን ሸዋ ቡልጋ ኢቲሳ ውስጥ ይገኛል፡፡ አባ ኖብ በመከራ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ስማቸውን ቢጠራ ከመከራው ፈጥኖ እንደሚድንባቸው ከጌታችን ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ የበረከት አባት ናቸው፡፡ በጸሎታቸው ይማረን! + + +

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ