ቅዱስ አባ አቡናፍር



 በገድል ከመጠመዱ የተነሣ ጥቂት የሰሌን ፍሬዎችን ብቻ እየተመገበ በበረሃ ውስጥ 60 ዓመት የኖረው ታላቁ ጻድቅ አቡነ አቡናፍር ታሪክ በትንሹ ይህ ነው፡፡

 እርሱም በእነዚህ ድፍን 60 ዓመታት ውስጥ የሰውን ፊት ከቶ አላየም፤ ይኽም ቅዱስ ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ ታላቅ አባት ነው፡፡

 ከላይኛው ግብፅ የተገኘ ሲሆን ታሪኩን የተናገረለት ጻድቁ አባ በፍኑትዮስ ነው፤ ይኸውም አባ በፍኑትዮስ ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ምንጣፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን የኖረ ነው፡፡

  ይህም ቅዱስ አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ በመመንኮስ በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋ በታላቅ ተጋድሎ ኖረ፤ ያማረ የምንኩስናውንም ሥራ በፈጸመ ጊዜ መነኮሳት ከሚኖሩበት ገዳም ርቆ ወደሚገኝ በረሃ ውስጥ ይገባ ዘንድ የከበሩ ገዳማውያንንም ይጎበኛቸው ዘንድ ለሚያነቧት ረብ ጥቅም ትሆን ዘንድ ገድላቸውንም እንዲጽፍ እግዚአብሔር አዘዘው፤ ለእግዚአብሔርም ትእዛዝ ራሱን ዘንበል አድርጎ ወደ ውስጠኛው በረሃ ገባ፡፡

  በዱር መካከልም ሲዞር ከከበሩ ገዳማውያን መካከል ብዙዎችን አገኛቸውና ዜናቸውን ተረድቶ ገድላቸውን ጻፈ፤ ገድላቸውንም ከጻፈላቸው እጅግ የከበሩ ቅዱሳን መካከል አባ ጢሞቴዎስና አባ አቡናፍር ይገኙበታል፡፡

  በአንዲት ዕለት አባ በፍኑትዮስ ወደ እርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍር አየው፤ አባ በፍኑትዮስም የሰይጣንን ምትሐት የሚያይ መስሎት ደነገጠ፤ አባ አቡናፍር ፀጉሩና ጽሕሙ ሰውነቱን ሁሉ ሸፍኖታል እንጂ በላዩ ላይ ልብስ አልነበረውም፡፡

 አባ በፍኑትዮስንም በመስቀል ምልክት ባርኮ አጽናናው፤ አቡነ ዘበሰማያትንም ከጸለየ በኋላ ‹‹አባ በፍኑትዮስ ሆይ ወደዚህ መምጣትህ መልካም ነው›› ብሎ በስሙ ከጠራው በኋላ ፍርሃቱን አራቀለት፡፡

  ከዚህም በኋላ ሁለቱም በጋራ ጸልየው የእግዚአብሔርን ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ፤ አባ በፍኑትዮስም አኗኗሩንና እንዴት ወደዚህ በረሃ እንደመጣ ታሪኩን ይነግረው ዘንድ አባ አቡናፍርን ለመነው፡፡

  አባ አቡናፍርም ታሪኩን እንዲህ ብሎ ነገረው

‹‹እኔ ደጋጎች እውነተኞች መነኮሳት በሚኖሩበት ገዳም ውስጥ እኖር ነበር፤ የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኗቸውም ሰማሁ፡፡

   እኔም ‹ከእናንተ የሚሻሉ አሉን?› ብዬ ጠየኳቸው፤ እነርሱም ‹አዎን እነርሱ በበረሃ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው፤ እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆንን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን፣ በበረሃ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው› አሉኝ፡፡

   ይህንንም ስሰማ ልቤ እንደ እሳት ነደደና ወደ ፈቀደው መንገድ ይመራኝ ዘንድ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ጸለይኩ፤ ከዚህም በኋላ ተነሥቼ ወጥቼ ስጓዝ አንድ አባት አገኘሁና የገዳማውያንን ገድላቸውን እያስተማረኝ ከእርሱ ጋር ተቀመጥኩኝ፡፡

   ከዚያም ወደዚህ ቦታ ደረስኩ፤ እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝን ይህችን ሰሌን አገኘኋት፤ በየዓመቱ 12 ዘለላ ታፈራለች፤ ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚህች ምንጭ እጠጣለሁ፡፡

  በዚህችም በረሃ እስከዛሬ 60 ዓመት ኖርኩ፤ ከአንተም በቀር የሰው ፊት ከቶ አይቼ አላውቅም›› ብሎ አቡነ አቡናፍር ጣፋጭ ታሪኩን በዝርዝር ነገረው፡፡

  ይህንንም ሲነጋገሩ የታዘዘ መልአክ መጥቶ የጌታችንን ሥጋና ደም አምጥቶ አቆረባቸው፤ ቀጥለውም ጥቂት የሰሌን ፍሬ ተመገቡ፤ ወዲያውም የአቡነ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ሆነ፡፡

  ወደ እግዚአብሔርም በተመስጦ እየጸለየ ሳለ ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፤ አቡነ በፍኑትዮስም በፀጉር ልብሱ በክብር ገንዞ ቀበረው፡፡

  ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ ወደደ ነገር ግን ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች፤ የውኃዋም ምንጭ ደረቀች፡፡

  አባ በፍኑትዮስም ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የአባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆነ፡፡

እንግድ የአባቶቻችን ታሪክ/ገድል / ብዙ ነው፡ ተነግሮም አያልቅም!

የአቡነ አቡናፍርና የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን!🙏

               "አሜን!"

No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ