አቡነ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት

 


‹‹በጎርጎርዮስ›› ስም የሚጠሩ ብዙ እጅግ የከበሩ ታላላቅ ቅዱሳን አሉ፡፡

🎚ከእነዚህም ውስጥ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ አቡነ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ራእዩ ህቡአት፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘላዕላይ ግብፅ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ እና ሌሎችም ብዙዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ኅዳር 21 ቀን የዕረፍቱን በዓል የምናከብርለት አቡነ ጎርጎርዮስ

ገባሬ መንክራት የተባለውን ነው፡፡

‹‹ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት›› የተባለው አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ስለሚታወቅ ነው፡፡

ሀገሩ ሮም ነው በዚህም ምክንያት ጎርጎርዮስ ዘሮም እየተባለም ይጠራል፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ ብሉይንና ሐዲስን ጠንቅቆ የተማረ ሲሆን

በሌላም በኩል ሕግ አዋቂና ተርጓሚ ሊቅ ስለነበር አንድ ቀን

ለተበደለ ድኃ ሊከራከርለት ሲሄድ በመንገድ ላይ ሳለ መልአክ ጠርቶት ወደ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡

ከብዙ ቆይታውም በኋላ

አረጋዊው የሀገሪቱ ኤጲስ ቆጶስ በሥራው እንዲራዳው በማሰብ

‹‹እኔን እርዳኝ፣ አንተ ተሾምና ገዳሙን አግልግል›› ቢሉት

ሹመቱንና ውዳሴ ከንቱን አልፈልግም በማለት እምቢ አላቸው፡፡

አረጋዊው ኤጲስ ቆጶስም ግድ ቢሉት ሸሽቶና ተደብቆም ገዳም

ገብቶ በተጋድሎ መኖር ጀመረ፤ ኤጲስ ቆጶሱም ካረፉ በኋላ

ማንን እንደሚሾሙ ሲመካከሩ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ

ለመነኮሳቱ ‹‹የመለኮትን ነገር የሚናገር ገዳማዊ ጎርጎርዮስን

ፈልጋችሁ ሹሙት›› ብሏቸው ተሰወረ፡፡

እነርሱም ሲፈልጉት አጥተውት ሲጨነቁ መልአኩ ድጋሚ ተገልጦ የክብር ልብሱን ሰጣቸው፡፡

መነኮሳቱም ወንጌልንና ልብሱን ከወንበሩ ላይ አኑረው እየጸለዩ እርሱ በሌለበት ሾሙት፡፡

ስሙንም ‹‹የመለኮትን ነገር በሚናገር በገዳማዊ ጎርጎርዮስ

ስም ጎርጎርዮስ›› ብለው ሰየሙት፡፡

ለእርሱም በበዓቱ ውስጥ

ሳለ የታዘዘ ብርሃናዊ መልአክ መጥቶ ‹‹ተነሥተህ ወደ እነርሱ

ሂድ፣ እነሆ በላያቸው ኤጲስ ቆጶስነት ሾመውሃልና፤ ይህም

ከእግዚአብሔር የሆነ ነው›› አለው፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስም ተነሥቶ

ሲሄድ በሌለበት በልብሱ ብቻ ሹመውት አገኛቸው፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስም ‹‹ሹመቱን አልፈልግም›› ብሎ ከብቃቱ የተነሣ በተአምር ከመካከላቸው ተሰውሮባቸው ሄደ፡፡

መልአኩም እየመራ ወስዶ ያለበትን ካሳያቸውና ለእርሱም ሹመቱ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን ነግሮት በሹመቱ እንዲጸና አድርጎታል፡፡

ከዚህም በኋላ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረገ ሲያገለግል ኖሯል፡፡

ሁለት ወንድማማቾች በጋራ የሚጠቀሙበትና ብዙ ዓሣዎች የሚጠመድበት አንድ ባሕር ነበር፡፡

እነርሱም በእኔ ይገባኛል ተጣልተው ባለመስማማት አቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ ሄዱ፡፡

አባታችንም ሊያስማማቸው ቢሉ ወንድማማቾቹ እምቢ

አሉ፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስም ባሕሩን በተአምራት አድርቆ የሚታረስ

መሬት አድርጎ ሰጣቸው፤ ወንድማማቾቹም ተካፍለው በማረስ በሰላምና በፍቅር ኖሩ፡፡

እግዚአብሔርም በአቡነ ጎርጎርዮስ እጅ ሌሎች ብዙ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን አደረገ፡፡

በዚህም ጻድቁ ‹‹ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

በስሙ አንድ ቅዳሴ አለው፣ ቅዳሴውም በዕለተ ሆሳዕና በዓል ይቀደሳል፤ ሃይማኖተ አበውና ሌሎቹም የሊቃውንት መጻሕፍት በስፋት የሚጠቅሱት ይህ ጻድቅ አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ በተወለደበትና በተሾመበት ዕለት ኅዳር 21 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡


በረከቱ ረድኤቱ ይድርብን

No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ