የቤተክርስቲያን አርማ


   ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አርማ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በአሉት 
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንዲውል ወ ሰነ ።ከዚህ በፊት ይህ አርማ በቅዱስ ሲኖዶስ ቅጥር ግቢ ብቻ አገልግሎት ይሰጥ ነበር።
ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አርማ እንጂ ሰንደቅ ዓላማ አይደለም፡፡ ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ የሚወሰነው በፓርላማ ወይም በሕዝበ ውሳኔ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ባንዲራ ወይም ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን አርማ ነው ያወጣችው እርሱም በ፳፻፯ዓ.ም. በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፬ ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ ፬ የቤተ ክርስቲያን ዓርማ፤
፩.የዓርማው ቅርጽና ይዘት፤
፩፥፩.መደቡ ነጭ፡፡
፩፥፪.ዙሪያው የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ፡፡
፩፥፫.ከላይ ከአናቱ አክሊል፤ ከታች ከግርጌው መሐል ለመሐል ወጥቶ አናቱ ከአክሊሉ ሥር የደረሰና መስቀል ያለበት አርዌ ብርት፡፡
፩፥፬.በግራ ኹኖ በቀኝ እጁ አርዌ ብርት፤ በግራ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፤ በቀኝ ኹኖ በግራ እጁ አርዌ ብርት በቀኝ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፡፡
፩፣፭.ከአርዌ ብርቱ ሥር «ነዋ ወንጌለ መንግሥት» ተብሎ የተጻፈበት ቅዱስ መጽሐፍ፡፡
፩፥፮.ከቅዱስ መጽሐፍ ሥር መስቀለኛ የ «ጸ» ፊደል ቅርፅን የሚመስል፤ ኹለቱ ጫፎቹ ከመደቡ ወደ ውጭ የወጣ ሰበን፡፡
፩፥፯.የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ በተገናኙበት የዓለም ምስል፤ ያለበት ይኾናል፡፡

፪.የዓርማው ትርጉም፤
፪፥፩.መደቡ ነጭ መኾኑ፦ ዘመነ ሥጋዌ የምሕረት የደስታና የነፃነት ዘመን መኾኑን ያመለክታል።
(ዮሐ.፳፥፲፪፤ የሐዋ. ሥራ ፩፥፲)
፪፥፪.የዓርማው ዙሪያ በወይን ዛላና በስንዴ ዘለላ የተከበበ መኾኑ፦ ምእመናን በቅዱስ ቊርባን አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን፥ ስርየተ ኃጢአትን፥ የዘለዓለም ሕይወትን የሚያገኙ መኾናቸውን ይገልጻል።
(ዮሐ.፮፥ ፶፫-፶፰፤ ማቴ.፳፮፥፳፮-፳፱፤ መዝ.፬፥፯)
፪፥፫.በዓርማው መሐል ቀጥ ብሎ የቆመ የዓርዌ ብርት ምስል በበላዩ ላይ መስቀል ከዚያም ከፍ ብሎ አክሊለ ክህነት አለው የዚኽ ትርጉም፦ ሕዝበ እስራኤል ዓርዌ ብርቱን ባዩ ጊዜ ከእባብ መርዝ እንደ ዳኑ ኹሉ መስቀል ላይ በተሰቀለ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ኹሉ በዲያቢሎስ ምክንያት ከመጣባቸው ፍዳ ኃጢአት የሚድኑ መኾናቸውን መስቀሉ የቤተ ክርስቲያን የድኅነት ዓርማ መኾኑን።
(ዘኍ.፳፩፥፰፤ ዮሐ.፫፥፲፬)
፪፥፬.አክሊል፦ ቅዱሳን በሰማያዊ መንግሥት የሚቀዳጁትን አክሊለ ክብር እና ማኅተመ ጽድቅን ያመለከታል።
(ዘጸ.፴፱፥፴፤ ፩ተሰ.፪፥፲፱፤ ፪ጢሞ. ፬፥፰፤ ፩ጴጥ.፭፥፲፬፤ ራእይ ፪፥፲፤ ፬፥፲፬)
፪፥፭.ኹለት መላእክት የዘንባባ ዝንጣፊና ዓርዌ ብርቱን ይዘው ይታያሉ ይህም ዘንባባ፦ በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መንፈሳዊ ደስታንና ድኅነተ ነፍስን ያመለክታል ቅዱሳን መላእክት የቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎችና የመልካም ዜና አብሣሪዎች መኾናቸውን ያሳያል ዓርዌ ብርቱን ይዘው መቆማቸው ነገረ መስቀሉን አምኖና ሃይማኖቱን አጽንቶ ይዞ የሚኖር የዘለዓለም ድኅነትን የሚያገኝ መኾኑን ያመለክታል።
(መዝ.፺፥፲፩፤ ሉቃ.፲፫፥፮-፱፤ ዕብ.፩፥፲፬)
፪፥፮.የዓርማው መሀል ቅዱስ መጽሐፍ ሆኖ፦ «ነዋ ወንጌለ መንግሥት» የሚል ጽሑፍ በበላዩ አለበት የዚኽ ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት ቀኖና እና ትውፊት በቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መኾኑን ያመለክታል፡፡
(ማቴ.፳፬፥፲፬)
፪፥፯.የወይኑ፦ የስንዴው ዛላና ዘለላ በተገናኙበት ላይ የሚታየው ክብ ነገር፥ ዓለምን የሚወክል ኾኖ ዓለም በክርስቶስ መዳኑን ያመለክታል፡፡
(ዮሐ.፫፥፲፯)
፫.የዓርማው ክብር፤
፫፥፩.ዓርማው፦ የቤተክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ ክብር መገለጫ ስለኾነ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር የሚገኙ ቤተክርስቲያን መዋቅር አካላት በሙሉ ከዚኽ ዓርማ በቀር ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡
፫፥፪.የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ደብዳቤ ሆኖ ይህ ዓርማ የሌለበት ማኅተምና የማዘዣ የሚጠቀም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጽ/ቤት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !
ምንጭ :- ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፬

No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ