አርባዕቱ እንስሳ
የኃያሉ እግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ የአርባዕቱ እንስሳ በዓል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በኅዳር ወር ስምንት ቀን ይከበራል፡፡ እነዚህም መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው፤ ስለ እርሳቸውም ወንጌልን የጻፈ ዮሐንስ እንዲህ ሲል እንደመሰከረ ‹‹በዚያ ዙፋን ፊት በረድ የሚመስል ባሕር አለ፤ በዙፋኑም ዙሪያ አራት እንስሶች አሉ፤ በፊትም በኋላም ዓይንን የተመሉ ናቸው። የፊተኛው አንበሳ ይመስላል፤ ሁለተኛውም ላም ይመስላል፤ ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል፤ አራተኛውም የሚበር አሞራ ይመስላል። የእነዚህም የአራቱ እንሰሶች እያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው፤ ሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፤ የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽኑዕ ክቡር ልዩ ነው፤ እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም።››
ሁለተኛውም ስለ እርሳቸው ኢሳይያስ እንዲህ አለ፤ ‹‹ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኦዝያን በሞተ ጊዜ አሸናፊ እግዚአብሔርን ሰፊ በሆነና ከፍ ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ብርሃኑም ቤቱን መልቶ ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው አየሁት።
የአንዱም የአንዱም ክንፋቸው ስድስት ነው፤ በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን በሁለቱ ክንፋቸው እግሮቻቸውን ይሸፍናሉ፤ በሁለቱ ክንፎቻቸው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበራሉ፤ አንዱም አንዱም ከአንዱ ጋራ ‹‹ፍጹም አሸናፊ የሆንክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በምድርና በሰማይ የመላ ነው›› እያሉ ያመሰግናሉ።
ነቢይ ዳዊትም ‹‹በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ›› አለ፤ ‹‹ሁለተኛም በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ እርሱ ምድርን አናወጻት›› አለ።
ሕዝቅኤልም እንዲህ አለ፤ ‹‹ከወደ ሰሜን እነሆ ጥቅል ነፋስ ሲመጣ አየሁ፤ ታላቅ ደመና አለ፤ በዙሪያውም ብርሃን አለ፤ ከእርሱም እሳት ቦግ ብሎ ይወጣል። በደመናውም መካከል ባለ በእሳቱ ውስጥ እንደ አራት ራስ አሞራ መልክ የሚመስል አለ፤ በመካከሉም እንደ አራቱ ኪሩቤል መልክ ያለ አለ፤ መልካቸውም እንዲህ ነው፤ በውስጣቸው የሰው መልክ አላቸው፤ የአንዱም የአንዱ ፊቱ አራት ነው፤ ክንፉም አራት ነው። እግራቸውም የቀና ነው፤ ከእግራቸውም ክንፍ አላቸው ሰኮናቸው ግን እንደ ላም ሰኮና ነው፤ ከእርሱም እሳት ቦግ ይላል፤ እንደጋለ ብረት ፍንጣሪም ይበራል።››
ወንጌላዊ ዮሐንስም ዳግመኛ እንዲህ አለ፤ ‹‹በዚያው ዙፋን ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ የእንስሶቹንም የእነዚያ አለቆችንም ቃል ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም እልፍ አለቆች ያሉአቸው ብዙ የብዙ ብዙ ነው። ለዚያ ለተገደለው በግ ኃይልን፣ ባለጸግነትን፣ ጥበብን፣ ጽናትን፣ መንግሥትን፣ ክብርን፣ ጌትነትን፣ ምስጋናን ገንዘብ ሊያደርግ ይገባዋል ብለው በታላቅ ቃል ተናገሩ። በሰማይና በምድር ከምድር በታች በባሕር ውስጥ በእነዚያም ውስጥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ጌትነት ክብር ኃይል በረከት በዙፋኑ ለተቀመጠው ለእርሱ ለበጉም ለዘላለሙ ይገባዋል አሉ፤ በእውነት ይገባዋል፤ እነዚህም አራቱ እንስሶች አሜን ይላሉ፤ እነዚያም አለቆች ይሰግዳሉ።››
ስለ ልዕልናቸውና ስለ ክብራቸው ለእነዚህ አርባዕቱ እንሰሳ ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል፤ መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው።
ዳግመኛም እንዲህ ተባለ፤ ‹‹ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፤ ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል፤ ገጽ ላሕም ስለ እንስሳ ይለምናል፤ ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል፤ ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና።››
ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነፁ በዚችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ፤ እነርሱ ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና።
እግዚአብሔር አምላካችን በቅዱሳን አርባዕቱ እንስሳ አማላጅነት ይማረን፤ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን።
ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...
በብዙ አንባቢያን የተነበቡ
-
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን ጻድቁ አባ ጳውሊ ዲያብሎስን ገዝተውት ሳለ ብዙ የሚያስትባቸውን ምሥጢራት በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ እኔም ሐይቅ ቅዱስ እ...
-
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አርማ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በአሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንዲውል ወ ሰነ ።ከዚህ በፊት ይህ አርማ በቅዱስ ሲኖዶ...
-
ክፍል ሦስት ‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል) ‹‹ዳግመኛም ሕዝቡን፣ ቀሳውስቱን፣ ካህናቱን፣ ሊቃውንቱን እንዲነቅፉ አደርጋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ከጽድቅ ሥራ ሰንፈው ለኃጢአት ሥ...
-
በሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ ‹ቅዱሳን› ማለት ‹የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐን የኾኑ፣ የጠሩ› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና የጌትነቱ መገለጫ የኾኑ ዂሉ ቅዱሳን ይባላ...
-
የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገ...

No comments:
Post a Comment