" ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።"
ዮሐ. ፲፬፥፰ /14፥8/
ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው ፊልጶስ ከገሊላ የተገኘ የቤተ ሳይዳ ሰው ነው
ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤልን "የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል መጥተህ እይ" በማለት ከክርስቶስ ጋር አገናኝቶታል በዚህም ናትናኤል በክርስቶስ ሐዋርያ ሆኖ መመረጡን ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን። ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ከኢየሱስ ክርሰቶስ ጋር እየተከተለ ወንጌልን ተማረ ብዙ ድንቆችንም ክርስቶስ ሲፈጽም ለማየት በቃ።
ኢየሱስ ክርስቶስን አብን አሳየን ብሎ በመጠየቁ ክርሰቶስም "እኔን ያየ አብን አየ፤ እስከዛሬ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን" ብሎ መልሶለታል (ዮሐ. 14፥9)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ወንጌልን እየሰበከ ብዙዎችን ከጣኦት አምላኪነት ወደ ክርስትና አምጥቷል። ፍሬግያ፣ ሰማርያና ጋዛ በሚባሉ አከባቢዎች እየተዘዋወረ የክርስቶስን ጌትነት፣ የወንጌልን እውነት አጉልቶ አሳይቷል።
ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ታናሽዋ እስያ በመሄድ በሄራፖሊስ ከተማ እያስተማረ ብዙዎችን በማሳመኑ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ይዘው አሰቃዩት፣ አንገላቱትም።
ከብዙ እንግልትም በኋላ በህዳር ፲፰ /18/ ቀን በመስቀል ላይ ሰቅለውት መስዋዕትነትን ተቀበለ። የሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ምልጃና በረከት በእኛ ላይ ይደር። ጸሎቱ ከእኛ አይለይ።
አሜን!

No comments:
Post a Comment