ክፍል ሦስት ‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል)



ክፍል ሦስት
‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል)
‹‹ዳግመኛም ሕዝቡን፣ ቀሳውስቱን፣ ካህናቱን፣ ሊቃውንቱን እንዲነቅፉ አደርጋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ከጽድቅ ሥራ ሰንፈው ለኃጢአት ሥራ እንዲተጉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ንስሓ እንዳይገቡ በውስጣቸው ፍርሃትን፣ ትምክህትን፣ ስንፍናን አሳድርባቸዋለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት የወንድሞቻቸውን
ኃጢአት እንጂ የራሳቸውን ኃጢአት አይናዘዙም፡፡ በዚህም ምክንያት ለበደላቸው ሥርየት የላቸውም፡፡ ከኃጢአት እንዳይርቁ በእነርሱ ላይ የማላመጣው ምክንያት የለም፡፡ ምክሬን ከሰሙኝ ፈጽሜ የክርስቶስን ጸጋ አሳጣቸዋለሁ›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ አለቀሰ፡፡ ሰይጣንም አባ ጳውሊ ሲያለቅስ ባየ ጊዜ ደስ አለው፡፡ ይስቅበትም ጀመር፡፡ ‹‹እንደ አንተ ካህናት ናቸውና ስለእነርሱ ታለቅሳለህን?›› አለው፡፡ ‹‹በእውነት ማልቀስ ከወደድክ ስለሊቃውንት፣ ስለደጋግ ነገሥታትና ሥልጣናት፣ ስለመኳንንት፣ ስለገዥዎች መታጣት ፊትህን ጸፍተህ አልቅስ፡፡ ዳግመኛም ስለንጹሐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስለኤጲስቆጶሳት፣ ስለቆሞሳትና ስለደጋግ ንጹሐን ካህናት መታጣት አልቅስ፡፡ አብዝተህ ስለቤተ ክርስቲያን በገዳም ስለሚኖሩና ስለገዳማትም አልቅስ፡፡ ይልቁንም ስለወንድሞችህ መነኮሳትን ስለእኅቶችህ መነኮሳይያት ፈጽመህ አልቅስ በኋላ ዘመን ዘመዶቼና ወዳጆቼ አደርጋቸዋለሁና›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ፈጽሞ እያዘነ ‹‹በምን ሥራ እንዲህ ታደርጋቸዋለህ?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ‹‹እነርሱ ራሳቸው በፈቃዳቸው ጎዳናዬን ሁሉ ይከተላሉ፣ ፈቃዴንም ይሠራሉ፡፡ የማሳስባቸውንም ይሠራሉ፣ ቃሌንም አይተላለፉም›› አለው፡፡

ቅዱስ አባ ጳውሊም ይህንን የሰይጣንን ነገር በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን አዘነ፡፡ ሰይጣንንም ‹‹አንተ የተረገምክ ክፉ ርኩስ የሆንክ እነሆ ሌላ ምክንያት እጠይቅሃለሁና እንዳትሸሽገኝ አምልሃለሁ›› አለው፡፡ ሰይጣንም ታላቅና ኃያል የሆነ ብርሃንን በፈጠረ በእርሱ ማልኩ፤ ከአንተ ምሥጢሬን እንዳልሸሽግ አዟልና ልደብቅ ብወድ አልቻልኩም፣ ምንም ልደብቅህ ልዋሽህ አልችልም›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹በውኃ ምንጮች እንደምታድሩ ሰዎች የሚናገሩት እውነት ነውን?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹አዎን እውነት ነው›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹በውኃ ምንጮቹ የምታድሩት በምን ምክንያት ነው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹የፈጣሪያቸውን ሕጉንና ትእዛዙን ቢያፈርሱና ስሙን ባይጠሩና የእኛን ፈቃድ ቢፈጽሙ ነው፡፡ በመልካም ምግባር ሆነው በፍጹም ሃይማኖት የእግዚአብሔርን ስም ቢጠሩ ኃይል የለንም፡፡
እኛ ብዙ ዓይነት በሽታን አእምሮ ማጣትን ዕብደትን እናመጣለን፡፡ ሰውን ባሳመምነው ጊዜ ሄዶ በእኛ ስም ሲጠመቅ ከበሽታው ይድናል፡፡ በዚህም ስመ ክርስትናው ትጠፋለች፡፡ ሰዎችም የታመመው ሲድን ባዩና በሰሙ ጊዜ እኛን ያመልካሉ፡፡ ባላወቁትም መንገድ አሳስተን እናጠፋቸዋለን፡፡መንፈሳውያንን መንፈሳዊ በማስመሰል እናጠምዳቸዋለን፡፡ መንፈሳዊ በሚመስል ነገር የተጠመዱ ከእኛ አያመልጡም›› አለው፡፡
አባ ጳውሊም ‹‹አስቀድመህ ለነገሥታት፣ ለመኳንንት፣ ለታላላቆቹ ለመሳፍንት፣ ለሊቃውንት አልቅስ ያልከኝ ስልምድነው?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ‹‹ሹመታቸው ታላቅ እንደመሆኑ ኃጢአታቸውም ብዙ ነውና፡፡ በሹመት ራስን ከፍ ማድረግን፣ ውዳሴ ከንቱን፣ ትምክህትን፣ ትዕቢትን እናመጣባቸዋለን፡፡ ከሹመት መሻርን፣ መድከምን፣ ሞትን እንዳያስቡ እናደርጋቸዋለን፡፡ ቀናውን ፍርድ ትተው በመማለጃና በአድልዎ እንዲፈርዱ እናደርጋቸዋለን፡፡ የማስተዋል አእምሮአቸውን እናጠፋዋለን፡፡ እውነተኛውን ፍርድና ቀናውን መንገድ ይተዋሉ፡፡ ስለዚህ ዘወትር ድኆችንና ደካሞችን ያስለቅሳሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ እናርቃቸዋለን፡፡ ትምክህትን፣ ትዕቢትንና ገንዘብ መውደድን በልባቸው እናሳድርባቸዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት ጦርነት አስነሥተው እርስ በእርሳቸው ይጋደላሉ፤ የእነርሱ መከራ ለታላቁም ለታናሹም ለሀገሩም ሁሉ ይተርፋል፡፡ በኃጢአታቸውም ይጠፋሉ›› አለው፡፡
ቀጥሎም አባ ጳውሊ ዲያብሎስን ‹‹አንተ የተረገምክ በሊቃነ ጳጳሳት፣ በጳጳሳት፣ በኤጲስቆጶሳትስ ላይ ምን ምክንያት አግኝተህ ትዋጋቸዋለህ?›› አለው፡፡ ሰይጣንም መለሰ፣ እንዲህም አለ፡- ‹‹ከሁሉ አብልጠው ብርን ገንዘብን ወርቅን እንዲወዱ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ለማይገባው ሥልጣነ ክህነትም በገንዘብ እንዲሰጡ፣ ለነዳያን ለድኆች እንዳያዝኑ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ለሌላው የሚያስተምሩትን የሕግ ጎዳና እንዳያስተውሉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ዘወትር ኃላፊውን የምድር ተድላ ደስታ እንዲያስቡ አደርጋቸዋለሁ፡፡
ጠብን ጥላቻን በልባቸው አሳድራለሁ፡፡ አንዱ አንዱን ወንድሙን በቅናት እንዲከሰው አደርጋለሁ፡፡ ለጸሎት በቆሙ ጊዜ ጠባቸውን እንዲያስቡና ቂማቸውን እንዳይረሱዋት ባልጀራቸውን እንዲረግሙ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ኃላፊውን ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዲተጉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ የማሳያቸውን የልብስ ዓይነት ይለብሳሉ፡፡ ዳግመኛም በገዳም የሚኖሩትን መነኮሳት አብልጬ እጣላቸዋለሁ፡፡ የኅሊና ጦር አመጣባቸዋለሁ፡፡ ከእንቅልፍ በነቁ ሰዓት ወይም ለጸሎት ሲነሡ የውዳሴ ከንቱ፣ የቅንዓት፣ የትምክህት ሀሳቦችን አመጣባቸዋለሁ፡፡ ድካማቸውን ከንቱ አደርጋለሁ፡፡ በጸሎታቸውና በተጋድሎአቸው እንዳይጠቀሙ አደርጋቸዋለሁ፡፡ በበዓታቸው በአንድ ቦታ እንዳይጸኑ አደርጋቸዋለሁ፡፡ በሥራ ላይ ያሉትንም ሥራቸውን እንዲያመልኩና ‹እኔ እበልጣለሁ› እንዲሉ በዚህም ሥራቸው ትዕቢትን፣ ትምክህትን፣ ውዳሴ ከንቱን አመጣባቸዋለሁ፡፡ የዚህን ዓለም ተድላና ደስታ እንዲወዱ በማድረግ እዋጋቸዋለሁ፡፡ የውሸት ሕልም በማሳየት አሳስታቸዋለሁ፡፡ የመምህሮቻቸውን ትእዛዝ እንዳይቀበሉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ከልባቸው ትሕትናን፣ ታዛዥነትን የምትጠቅም የአበውን ምክር መስማትን አጠፋባቸዋለሁ፡፡ እንደመቃብር በውጫዊ ዕይታቸው ያማሩ በውስጣቸው ግን ኃጢአትን ርኩሰትን የተሞሉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ አንድ እንኳን ሳላስቀር ከእግዚአብሔር ቸርነት ፈጽሜ እስከማርቃቸው ድረስ ባለኝ አቅሜ ሁሉ እዋጋቸዋለሁ፡፡ እነሆ የጠየቅኸኝን ክፉ የሆነች የማሳስትባን ምሥጢሬንና የክፋት ሥራዬን ሁሉ ምንም ሳልደብቅ በአምላክህ ትእዛዝ በአንተም ግዝት ተይዤ ያለፈቃዴ በግዴ ነገርኩህ›› አለው፡፡
አባ ጳውሊም ‹‹ፈቃድህን ያደረጉ ክፉዎች ሰዎችን እንድታጠፋቸው የታዘዝክበት ጊዜ ደርሷልና በዚህ ዳንስ ቤት ፈቃድህን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ምን ለማድረግ ታስባለህ?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ለትእዛዝህ የተገዛሁ እንድሆን ተፈርዶብኛልና ጸሎትህ አስሮ ስለያዘኝ እስከ አሁንም ድረስ ቆይቻለሁና እንዳዘዝከኝ አደርጋለሁ›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹የታዘዝከውስ በዳንስ ቤት ያሉትን ፈቃድህን የፈጸሙትን ሰዎች እንድትገድላቸው ነው›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ለእነዚህ ሰዎች ግደላቸው የምትለኝ አታዝንላቸውምን? አንተ መንፈሳዊ የደጋጎች ወገን ነህና›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹ፈቃድህን ለሚፈጽሙ ሰዎች እንደማትጠቅማቸውና ምሕረት የሌለህ ክፉ መሆንህን ሌሎች ዐውቀው ከአንተ እንዲሸሹ ይህንን ጥፋት እንድታደርግባቸው እሻለሁና የታዘዝከውን ፈጥነህ አደርግ፡፡ ነገር ግን በወዳጆችህ ላይ ይህ ክፉ ሥራ እንደሠራህና እንደገደልካቸው ምስክር እንዲሆኑ ከእነርሱ 5 ሰዎችን አስቀር›› አለው፡፡ ሰይጣንም አባ ጳውሊን ‹‹እነዚህን ሰዎች ፈጥኜ አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ የዳንስ ቤት አካባቢ ርቀህ ሂድልኝ›› አለውና ሄደለት፡፡ ሰይጣንም መልኩን ለውጦ እንደሚነድ እሳት ሆኖ በሮ ሄዶ በዳንስ ቤቱ ውስጥ ያሉትን ከ3 ወንዶችና ከ2 ሴቶች በቀር ሁሉንም በክፉ አሟሟት ገደላቸው፡፡
አባ ጳውሊም ሲሄድ ‹‹የመላእክት አለቃ ሆይ! አገልጋይህን ከዚህ ሰይጣን እጅ አድን፣ አቤቱ ሰይጣን በእኔ ላይ እንዳይሰለጥን አትተወኝ…›› ብሎ ጸለየ፡፡ በዚህም ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለአባ ጳውሊ በሚያምር ጎልማሳ አምሳል ተገለጠለትና ‹‹እነሆ ከዚህ ርኩስ ከሆነው ጠላት እንድጠብቅህና እንዳድንህ ተልኬያለሁና የተባረክ ቅዱስ አባት ሆይ አትፍራ›› አለው፡፡ ዳግመኛም መልአኩ ለአባ ጳውሊ ‹‹የጠየከውን በሙሉ እውነቱን እንደነገረህ ዕወቅ፤ ክፉ ሥራውን ከአንተ ምንም አልሸሸገብህም፡፡ የነገረህን በሙሉ ለሰው ሁሉ እንዲደርስና ትምህርት እንዲሆን ጻፈው፡፡ ዲያብሎስ ይህን የነገረህን የክፋት ወጥመድ ሁሉ በዚህ ትውልድ አብዝቶ አያደርገውም ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ አብዝቶ ይፈጽመዋል›› አለው፡፡ አባ ጳውሊ መልአኩን ‹‹ሰይጣን በኋላ ዘመን ኃይሉንና ክፋቱን ማሳየትና መበርታት የሚችለው ስለምንድነው?›› አለው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም ለአባ ጳውሊ እንዲህ እያለ ይነግረው ጀመር፡- ‹‹በኋላ ዘመን የሰው ሁሉ ኅሊና በየጊዜውና በየሰዓቱ እግዚአብሔርን ከማሰብና ከመልካም ሥራ ሁሉ ስለሚርቅና ስለሚሰንፍ ነው፡፡ በኋላ ዘመን ብዙዎች የቀናች ሃይማኖታቸውን ትተው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአጋንንትን ትምህርት ይከተላሉ፡፡ (እዚህ ጋ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በግልፅ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ›› ያለውን ልብ ይሏል፡፡ 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡1፡፡) በኋላ ዘመን ሰዎች ራሳቸውን ወዳድ፣ የኃጢአትን ተድላ ደስታ የሚወዱና ከእግዚአብሔር ፍቅር የራቁ ይሆናሉ፡፡ ሁላቸውም ገንዘብ ወዳጆች ይሆናሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ ቢሰበስቡም አይበቃቸውም፤ እነርሱ ይበቃናል አይሉም፡፡ በሰማይና በምድር የተመሰገነ እግዚአብሔርንም ፈጽመው አያመሰግኑትም፡፡ በኋላ ዘመን ዘወትር እየተማሩ እየተገሠጹ እያለ አያስተውሉም፣ ከጥፋትም አይመለሱም፣ ዕውነትንም ፈጽመው አያቋትም፡፡ ብዙ መምህራንና መጻሕፍት በእነርሱ ዘንድ እያሉላቸው እነርሱ ግን የሀሰተኞች መምህራንን ትምህርት ለመስማት ገሥግሠው ይሄዳሉ፡፡ በኋላ ዘመን ሰው ሁሉ የማይጠቅም ተአምርንና ምልክትን ይፈልጋል፡፡ ሰዎችም ምልክት በመፈለጋቸው ምክንያት ሰይጣን የሚፈልጉትን በማስመሰል በምትሐት ያሳስታቸዋል፡፡ በብዙ ሰዎችም ልቡና ቁጥር ሥፍር የሌለው ብዙ እንክርዳድ ይዘራል፡፡ ይህም ትዕቢት፣ ኩራት፣ የምንዝር ጌጥ መውደድ፣ መመካት፣ ዝሙት፣ ቅንዓት፣ ቂም በቀል፣ መናፍቅነት፣ ስንፍና፣ ሌብነት፣ ነገረ ሠሪነት፣ ነፍስ መግደል፣ በነፍስም በሥጋም የሚያጸይፍ የኃጢአት ሱስን መውደድ ይህን የመሰለ ነው›› አለው፡፡ 
አባ ጳውሊም መልአኩን ‹‹ሰይጣን ‹ኃጢአትን ይሠራሉና ለወንድሞችህ መነኮሳት አልቅስ› ብሎ የነገረኝ እንዴት ነው የሚፈጸመው?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹አዎ በኋላ ዘመን ከመነኮሳት መካከል ተለይተው ኃጢአት የሚሠሩ አሉ፡፡ ኃጢአት የሚሠሩበትም ምክንያት ይህ ነው፡-
በቦታ ጥበት ምክንያት ከዋናው ጽሑፍ ተቆርጦ የቀረው ቀጣይ ጽሑፍ..... መልአኩም ‹‹አዎ በኋላ ዘመን ከመነኮሳት መካከል ተለይተው ኃጢአት የሚሠሩ አሉ፡፡ ኃጢአት የሚሠሩበትም ምክንያት ይህ ነው፡- ‹ወደ እግዚአብሔር ከምታደርሳቸውና የዘላለም ሕይወትን ከሚያገኙባት መልካም ሥራ ሁሉ ልቡናቸው ይርቃል፣ ይደክማልና ነው፡፡ የቀደሙ የአበው ቅዱሳንን ሕግና ሥርዓት አይጠብቁም፡፡ የአበው ቅዱሳን ጻድቃንም ሥርአዓታቸው ትሕትናና ታዛዥነት፣ ፍቅርና ሰላም፣ ጾምና ጸሎት፣ ጥሪት ቁሪት አለማበጀትና ገንዘብን አለመውደድ፣ ትዕግሥትን ማዘውተር ውዳሴ ከንቱን መጥላት፣ የነፍስና የሥጋ ንጽሕና ይህንንም የመሰለ ነው፡፡ በኋላ ዘመን የሚነሡ መነኮሳት ግን ተድላና ደስታን በመፈለግ ገዳማዊነታቸውን ይተዋሉ፡፡ ተጋዳዮችና ደጋጎች የሆኑ አባቶቻቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በሠሩላቸው ሥርዓት ጸንተው አይኖሩም፡፡ እነርሱም መነኮሳት ሲሆኑ ነገር ግን በገድል ጽሙዳን በሆኑ መነኮሳት ወንድሞቻቸው ላይ ይዘባበታሉ፡፡ ስለዚህ ያንጊዜ ገዳማትና አድባራት ይደክማሉ፣ ብዙዎችም ይጠፋሉ›› አለው፡፡ ዳግመኛም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለአባ ጳውሊ እንዲህ አለው፡- ‹‹በኋላ ዘመን ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሜ ብነግርህም ከሊቃ ጳጳሳትና ከካህናት፣ ከምእመናንና ከመነኮሳት መካከል በትዕግስታቸውና በመልካም ሥራቸው በሃይማኖታቸው ጸንተው የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዙን ጠብቀው የሚኖሩደጋጎች ንጹሐን እውነተኞችም አሉና በበደለኞችና በኃጢአተኞች ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ ምድራዊ የሥጋ አኗኗራቸውን አይተው በደለኞችን እንዳይከተሉ ነገር ግን ታግሰው ነፍሳቸውን እንዲያድኑ፣ ሌሎችንም መክረው አስተምረው በንስሓ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲመልሷቸው ለሚሰሙትና ለሚያነቡት ከኃጢአት ለመጠበቅ ለማስተዋል ለንጽሓ ነፍስና ሥጋን ለመጥቀም ረዳትና አጋዥ እንዲሆናቸው ጠላት ዲያብሎስ የነገረህን ሁሉ ጻፍ›› አለው፡፡ የሀገሪቱንም ሰዎች መክሮና አስተምሮ እንዲያጠምቃቸው ነገረው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ሰሎንቅያ ሰዎች ቢሄድ በመቅሰፍት ስለሞቱት ሰዎች ተሰብስበው ሲያለቅሱ አገኛቸው፡፡ ዲያብሎስም በመቅሰፍቱ የገደላቸው ሰዎች በሩካቤ ኃጢአት እርስ በእርሳቸው እንደተያያዙ ሙተው ስለተገኙ የሰሎንቅያ አገር ሰዎች እጅግ ደንግጠውና ፈርተው ነበር፡፡ አባ ጳውሊም ከመቅሰፍቱ የተረፉትን 5 ሰዎች ያዩትንና የሆነውን ሁሉ ለሀገሩ ሕዝብ እንዲመሰክሩ በማድረግ የሞቱትን ምሳሌ ጠቅሶ በንስሓ ካልተመለሱ እነርሱም በመቅሰፍት እንደሚጠፉ አስተማራቸው፡፡ በትምህርቱም አመኑ፡፡ አባ ጳውሊም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ካጠመቋቸው በኋላ በሃይማኖት አጸናቸው፡፡ የአባ ጳውሊ ጸሎቱና በረከቱ ከሰይጣን ተንኮልና ወጥመድ ሁላችንንም የጥምቀት ልጆች ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡፡ (ጻድቁ አባ ጳውሊ ሰይጣንን በግዝት ይዘው ብዙ ምሥጢርን እንዲያወጣ ካደረጉት በኋላ መልአኩ እንደነገራቸው ጻድቁ ምሥጢሩን ሁሉ ለእኛ ለልጆቻቸው ጽፈውልናል፡፡ ይህንችን የአባ ጳውሊን እጅግ ጠቃሚ የሆነች ድርሳን ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ አንድነት ገዳም ከብራናው ላይ በግእዝና በአማርኛ አሳትሞ አውጥቶታል፡፡ እኔ በጣም አሳጥሬና ቀንጨብ አድርጌ ነው ያረብኩላችሁ እንጂ ሙሉ መጽሐፉ 82 ገጽ ነው፡፡ ‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› በሚል ርዕስ ገዳሙ ያሳተማት የአባ ጳውሊ መጽሐፍ እጅግ ጠቃሚ ናትና በአካል ለገዳሙ ቅርበት ያላቸው ሰዎችን የምታውቋቸው ካላችሁ መጽሐፏን አስመጥታችሁ ትጠቀሙባት ዘንድ ወንድማዊ ምክሬ ነው፡፡ መጽሐፏ እዛው ገዳሙ ውስጥ ካልሆነ በቀር አ.አ ገበያ ላይም ሆነ የትኛውም ቦታ አትገኝም፡
                አምላከ ቅዱሳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ መዋዕለ ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን!!

No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ