ክፍል ሦስት
‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል)
‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል)
‹‹ዳግመኛም ሕዝቡን፣ ቀሳውስቱን፣ ካህናቱን፣ ሊቃውንቱን እንዲነቅፉ አደርጋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ከጽድቅ ሥራ ሰንፈው ለኃጢአት ሥራ እንዲተጉ አደርጋቸዋለሁ፡፡ ንስሓ እንዳይገቡ በውስጣቸው ፍርሃትን፣ ትምክህትን፣ ስንፍናን አሳድርባቸዋለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት የወንድሞቻቸውን
ኃጢአት እንጂ የራሳቸውን ኃጢአት አይናዘዙም፡፡ በዚህም ምክንያት ለበደላቸው ሥርየት የላቸውም፡፡ ከኃጢአት እንዳይርቁ በእነርሱ ላይ የማላመጣው ምክንያት የለም፡፡ ምክሬን ከሰሙኝ ፈጽሜ የክርስቶስን ጸጋ አሳጣቸዋለሁ›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ አለቀሰ፡፡ ሰይጣንም አባ ጳውሊ ሲያለቅስ ባየ ጊዜ ደስ አለው፡፡ ይስቅበትም ጀመር፡፡ ‹‹እንደ አንተ ካህናት ናቸውና ስለእነርሱ ታለቅሳለህን?›› አለው፡፡ ‹‹በእውነት ማልቀስ ከወደድክ ስለሊቃውንት፣ ስለደጋግ ነገሥታትና ሥልጣናት፣ ስለመኳንንት፣ ስለገዥዎች መታጣት ፊትህን ጸፍተህ አልቅስ፡፡ ዳግመኛም ስለንጹሐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስለኤጲስቆጶሳት፣ ስለቆሞሳትና ስለደጋግ ንጹሐን ካህናት መታጣት አልቅስ፡፡ አብዝተህ ስለቤተ ክርስቲያን በገዳም ስለሚኖሩና ስለገዳማትም አልቅስ፡፡ ይልቁንም ስለወንድሞችህ መነኮሳትን ስለእኅቶችህ መነኮሳይያት ፈጽመህ አልቅስ በኋላ ዘመን ዘመዶቼና ወዳጆቼ አደርጋቸዋለሁና›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም ፈጽሞ እያዘነ ‹‹በምን ሥራ እንዲህ ታደርጋቸዋለህ?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ‹‹እነርሱ ራሳቸው በፈቃዳቸው ጎዳናዬን ሁሉ ይከተላሉ፣ ፈቃዴንም ይሠራሉ፡፡ የማሳስባቸውንም ይሠራሉ፣ ቃሌንም አይተላለፉም›› አለው፡፡




