ህዳር 15 በምልጃው ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቀው በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው፣ በግብጻውያን ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው ስሙን ጠርተው የማይጠግቡት፣ ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ የሆነና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሚያደርግ፣ በተለይ ለታመመ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ ባለ በጎ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ የሆነው የቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ዕረፍቱ ነው።
ቅዱስ ሚናስ ከደጋግ ቤተሰቦች የተገኘ ሲኾን እናቱ ልጅ ስላልወለደች በእመቤታችን በዓል ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ተማፀነቻት ያን ጊዜ ከእመቤታችን ሥዕል አሜን የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ከዚያም ይኽነን ለባሏ ነገረችው እግዚአብሔርም የተባረከውን ልጅ በ285 ዓ.ም ሰጣት፤ ስሙንም ሚናስ ብለው ሰይመውታል ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት፡፡ እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በስፋት አስተማሩት፤ በአሥራ ሁለት ዓመቱ አባቱ ሲያርፍ ከሦስት ዓመት በኋላ እናቱ ዐርፋ ቅዱስ ሚናስ ብቻውን ቀርቷል፤ ከዚያም መኳንንቱም አባቱን ይወድዱት ስለነበር በአባቱ ፈንታ ምስፍናን እንደ ሾሙት ዜና ገድሉ ይናገራል፡፡
ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን በካደ ጊዜ ቅዱስ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገብቶ ተጋድሎን ጀመረ፤ ከዕለታት ባንዳቸው ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊልን ሲቀዳጁ ተመለከተ ከዚኽ በኋላ ወደ ከተማ ተመልሶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ መኰንኑ ቅዱስ ሚናስ በወገን የከበረ መኾኑን ያውቃልና ብዙ የሹመት ቃል ኪዳን ገባለት እርሱም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለይ እንደማይችል ነገረው።
ያን ጊዜ ብዙ ሥቃይና መከራ አደረሰበት በመጨረሻም ራሱን በሰይፍ እንዲቈርጡት አዝዞ ከክርስቶስ ቃል ኪዳን ተቀብሎ ህዳር 15 ቀን የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፤ በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ለሚጠሩት በምልጃው እጅግ ፈጥኖ ይደርስላቸዋል።
የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጅ ከሰማይ “ሚናስ ንኡድ ክቡር ነኽ፤ ከልጅነትኽ ዠምሮ የቅድስናን ሕይወት በመምረጥ ሦስት አክሊላትን ሰጥቼሃለሁ፤ አንደኛው ስለቅድስናኽ፣ ኹለተኛው ስለ ብቸኝነትኽ፤ ሦስተኛው ስለ ሰማዕትነትኽ” የሚል ድምፅን ከጌታችን ሰምቷል፡፡
ከዚያም መኰንኑ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ወደ እሳት እንዲጣል ቢያስደርግም እሳት ፈጽሞ ሥጋውን ሊነካ አልቻለም፤ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ባማሩ ልብሶች ገንዘው አኖሩት፤ የመርዩጥ አገር ሰዎች ሰራዊትን ሊያከማቹ ስለወደዱ ምልጃው ይረዳቸው ዘንድ የቅዱስ ሚናስን ሰውነት ወሰዱ፤ እነርሱም በባሕር በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያሉ አውሬዎች ከባሕር ወጥተው አንገታቸውን ወደ ሚናስ ሥጋ በዘረጉ ጊዜ ከሰውነቱ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጥላቸዋለች፤ ሰዎቹም ይኽነን አይተው በእጅጉ ተደንቀዋል፡፡
ወደ እስክንድርያ ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከርሳቸው ጋር ሊወስዱ ወድደው በግመል ላይ በጫኑት ጊዜ ግመሉ ከቦታው የማይነሣ ኾነ፤ ኹለተኛም ሌላ ግመል ቢጭኑ ርሱም የማይነሣ ኾነ፤ ስለዚኽ ዛሬ ድረስ የቅዱስ ሚናስ ሥዕል ሲሳል እነዚኽ ገመሎች አብረው ይሳላሉ፤ እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት ቦታ መኾኑን ዐውቀው የከበረ ሥጋውን በዚያው አኖሩት፤ ከዚያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለት ሰኔ 15 ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈጽሞ ብዙዎች ድንቆች ተደርገዋል።
በግብጽ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ቅዱስ ሚናስ ከጌታችን በተቀበለው ቃል ኪዳን በተማፀኑት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚደርስላቸው በእጅጉ ይወዱታል፤ በተለይ ከአቡነ ሺኖዳ በፊት ለነበሩት በቅድስና ሕይወታቸው ይታወቁ ለነበሩት ለአቡነ ቄርሎስ ቅዱስ ሚናስ ተገልጦላቸው እንደባረካቸው ይነገራል።
የቅዱስ ሚናስ በረከት ይደርብን!

.jpeg)
No comments:
Post a Comment