ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ
ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ፡- ምግባር ሃይማኖታቸውና እጅግ ጽኑ የሆነው ተጋድሎአቸው ‹‹አባ›› ተብለው እንዲጠሩ አደረጋቸው እንጂ ገና የ12 ዓመት ሕፃን ናቸው፡፡ በሰማዕትነት ያረፉት በተአምራት ካሳመኗቸው ከ190 ሺህ ማኅበርተኞቻቸው ጋር ነው፡፡ ከደቡባዊ ግብፅ ከንሂሳ ገዳም የተገኙ ታላቅ ሰማዕት ናቸው፡፡ በተወለዱ በ5ኛ ቀናቸው መልአክ ሲያነጋግራቸው ወላጆቻቸው አይተው በአንክሮ እያዩ አሳደጓቸው፡፡ የነበሩበት ዘመን የክርስቲያኖች ደም እንደ ውሃ በሚፈስበት በከሃዲው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ስለነበረ አባ ኖብ ወደ ሰማዕትነቱ በፈቃዳቸው ሔደው በከሃዲው ንጉሥ ፊት ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ሔዱ፡፡ ሲሔዱም አንድ ጻድቅ ‹‹አባ አትሒዱ›› ቢላቸው ‹‹የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ቁልፍ ልቀበል ነው የምሔደው›› ብለውት ሔዱና በከሃዲዎቹ ነገሥታት ፊት የአምላካቸውን ክብር መሰከሩ፡፡ የታሠሩ ክርስቲያኖችን በክርስቶስ ማመናቸውን እስከመጨረሻው አጽንተው የተዘጋጀላቸውን የጽድቅ አክሊል እንዲወርሱ ይመክሯቸው ነበር፡፡
አባ ኖብም የወላጆቻቸውን ሀብት ለድኆች መጽውተው ወደ ሰማዕትነቱ ሲሔዱ መኰንኑ አገኛቸውና ‹‹ክርስቶስን ክደህ ለጣዖቶቻችን ስገድ›› ቢላቸው ከንቱነቱን ነግረው አስተማሩት፡፡ በብዙ አሰቃቂ መከራዎችም በእጅጉ አሰቃያቸው፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ፈወሳቸውና ወደፊት የሚደርስባቸውን ነገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ አትሪብ በመርከብ ይዟቸው ሲሔድ በመርከቡ ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ በመስቀል ሥጋቸው እስኪቆራረስ ድረስ በብረት በትር አስገረፋቸው፡፡ መኰንኑም እርሳቸውን እያስገረፈ እርሱ ተቀምጦ ሊበላና ሊጠጣ በፈለገ ጊዜ እመገባለሁ ቢል ምግቡ ድንጋይ ሆነበት፡፡ የአሽከሮቹም ዐይን ታወረ፡፡ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከስቅላታቸው አውርዶ ቍስላቸውንም ፈውሶ ደማቸውን ጠረገላቸው፡፡ አባ ኖብም ጸልየው የታወሩትን ሰዎች የዐይናቸውን ብርሃን መልሰውላቸው አስተምረው ወደ ሃይማኖትም መለሷቸው፡፡ እነርሱም መስክረው ሰማዕት ሆነው ተሰይፈዋል፡፡
ወደ አትሪብም ከደረሱ በኋላ አባ ኖብን ግን ስቃዩ ይጥናባቸው ብለው በብረት ችንካሮች ቸንክረዋቸው በብረት አልጋ ላይ አድርገው እሳት አነደዱባቸው፣ በመጋዝም ሰነጠቋቸው፣ ሰውነታቸውን ቆራርጠው ጣሉት፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ አዳናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወሰዷቸውና ብዙ አሰቃዩአቸው፡፡ ለመርዛማ እባቦች ቢሰጧቸውም ምንም አልነኳቸውም ይልቁንም አንዱ እባብ ሔዶ በመኰንኑ አንገት ላይ ተጠምጥሞ ነድፎ ለሞት አደረሰው፡፡ ሟርተኞቹ እንዳላዳኑት ካወቀ በኋላ አባታችን እባቡን ከአንገቱ ላይ እንዲወርድ አድርገው ፈወሱት፡፡
መኰንኑም ዳግመኛ በእሳት እንዲያቃጥሏቸው ቢያዝም እሳቱ እሳቸውን ማቃጠልን እምቢ አለ፡፡ መኰንኑ ማሰቃየቱ በሰላቸው ጊዜ አንገታቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ አባ ኖብ ስለ ክርስቶስ እየመሰከሩ ጽኑ መከራን እየተቀበሉ ለብዙ ዓመታት ከተሰቃዩና ከጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ሐምሌ 24 ቀን አንገታቸውን ተሰይፈው ሰማዕትነታቸውን ፈጽመዋል፡፡ 190 ሺህ ሰማንያ አራት የአባ ኖብ ማኅበርተኞችም እንዲሁ በሐምሌ 24 ተሰይፈው ሰማዕት ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ሺዎቹ በዛሬዋ ዕለት በዓመታዊ በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡
የሰማዕቱ የአባ ኖብ ቤተ ክርስቲያናቸው በአገራችን ሸዋ ቡልጋ ኢቲሳ ውስጥ ይገኛል፡፡ አባ ኖብ በመከራ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ስማቸውን ቢጠራ ከመከራው ፈጥኖ እንደሚድንባቸው ከጌታችን ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ የበረከት አባት ናቸው፡፡ በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...
በብዙ አንባቢያን የተነበቡ
-
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን ጻድቁ አባ ጳውሊ ዲያብሎስን ገዝተውት ሳለ ብዙ የሚያስትባቸውን ምሥጢራት በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ እኔም ሐይቅ ቅዱስ እ...
-
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አርማ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በአሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንዲውል ወ ሰነ ።ከዚህ በፊት ይህ አርማ በቅዱስ ሲኖዶ...
-
ክፍል ሦስት ‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል) ‹‹ዳግመኛም ሕዝቡን፣ ቀሳውስቱን፣ ካህናቱን፣ ሊቃውንቱን እንዲነቅፉ አደርጋለሁ፡፡ ሁላቸውንም ከጽድቅ ሥራ ሰንፈው ለኃጢአት ሥ...
-
በሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ ‹ቅዱሳን› ማለት ‹የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐን የኾኑ፣ የጠሩ› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና የጌትነቱ መገለጫ የኾኑ ዂሉ ቅዱሳን ይባላ...
-
የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገ...
No comments:
Post a Comment