አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጻድቁ አባ ጳውሊ ዲያብሎስን ገዝተውት ሳለ ብዙ የሚያስትባቸውን ምሥጢራት በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ እኔም ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ አንድነት ገዳም ‹‹ተዋሥኦተ
ቀሲስ አባ ጳውሊ››
በሚል ርዕስ ያሳተማትን የአባ ጳውሊን ምሥጢር የያዘች እጅግ ድንቅ የሆነች መጽሐፍን ካሁን በፊት በሁለት ክፍል አቅርቤው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ክፍል እናያለን፡፡ ነገር ግን በዚህ የጌታችን ታላቅ ጾም ወቅት ጽሑፉ እጅግ ጠቃሚ ከወቅቱም ጋር የሚሄድ ነውና ላላነበቡትም እንዲሆን በማሰብ ከክፍል አንድ ጀምሬ ሦስቱንም ክፍሎች በየተራ እነሆ፡- በቅድሚያ ግን ሲነገሩ ብዙ ጊዜ ብንሰማቸውም አባ ጳውሊ ከሚነግሩን ምሥጢራት ጋር የተስማሙ ይሆኑልን ዘንድ እስቲ እነዚህን ቀጥሎ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በደንብ አጢነን እንመልከታቸው፡፡ መልእክታቸውም ምን እንደሆነ በደንብ እንረዳው፡፡
‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ ›› 1ኛ ጴጥ 5፡8፡፡
‹‹እነሆ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፡፡ ›› ሉቃ 22፡31፡፡
‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፣ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና፡፡ ›› 1ኛ ዮሐ 3፡8፡፡
‹‹ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው? ›› 1ኛ ጴጥ 4፡18፡፡
‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፣ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፡፡ ›› ዮሐ 16፡33፡፡
‹‹ዓለምንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ ተጣለ፣ …ለምድርና ለባሕር ወዮቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው ዐውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዷልና፡፡›› ራእይ 12፡፡
ሰይጣን በአባ ጳውሊ ተገዝቶ ሳለ ያወጣው ምሥጢር ይህ ነው፡- በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ አንድነት ገዳም ያስተላለፈው አጭር መልእክት እንዲህ ይላል፡- ‹‹… ምእመናን የሰይጣንን ክፉ ሥራ ሁሉ ዐውቀውና ተረድተው ከሰይጣን ስሕተት እንዲጠበቁና እንዲማሩበት እንዲሁም ደግሞ ፈተና በሚመጣባቸው ጊዜ ፈተናው የመጣው ከሰይጣን ከሰይጣን መሆኑን ተረድተው ራሳቸውን ለፈተናው እንዲያዘጋጁና በየጊዜውም ራሳቸውን እንዲፈትሹ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው በማመን ይህን መጽሐፍ በገድሉና በትሩፋቱ ከከፍተኛ የቅድስና ደረጃ ላይ የደረሰውን የቀሲስ አባ ጳውሊን የሰይጣንን ምሥጢር ያጋለጠበትን ድርሳን ከብራናው ገልብጠን ግእዙን ወደ አማርኛ ተርጉመን ምእመናን በቀላሉ እንዲረዱት በሚያስችል ሁኔታ በእግዚአብሔር አጋዥነት አቅርበናል፡፡››
ልዩ ስሟ ሰሎንቅያ በምትባል በምስር አገር እንዲህ ሆነ፡- የከተማይቱ ሰዎች ከሄሮድስ ወገን የሚሆኑ ኃጢአተኞችና ክፉዎች ነበሩ፡፡ ሴቶችም ወንዶችም ተሰብስበው በየጊዜው በየወሩ ወደ ጭፈራ ቤት የመግባት ክፉ ልማድ ነበራቸው፡፡ መነኩሴ የሆነው ቅዱስ አባ ጳውሊም ዕድሜው 15 ዓመት
የሆነው አንድ ዲያቆን መነኩሴን አስከትሎ ከዚያች አገር ደረሰ፡፡ ቀኑም ረቡዕ ነበር፡፡ በዚህችም ቀን የሀገሪቱ ሰዎች ሴቶቹም ወንዶቹም ተሰብስበው ወደ አንዲት ጭፈራ ቤት ሲሄዱ አባ ጳውሊ ባደረበት የእግዚአብሔር ጸጋ የሰዎቹን ኃጢአት በግልጽ የሚያይ ሆነ፡፡ ከሰዎቹም አንዱን ጠርቶ ‹‹ይህን
ክፉ ሥራ ለምን ትሠራላችሁ? ወደ ዳንስ ቤትስ ከሚስቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር ለምን ትገባላችሁ?›› አለው፡፡ ሰውየውም ‹‹በመኝታችን
ከሚስቶቻችን ጋር አንድ እንደምንሆን በዳንስ ቤትም ከሴቶች ጋር አንድ እንሆናለን››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹ማንን
እንደምታመልኩ እስቲ ንገረኝ?›› ሲለው ሰውዬውም ‹‹ከሄሮድስ
ወገን ነን፣ የምናመልከውም ከቀደሙ አባቶቻችን ያገኘነውን ጣዖት ነው››
አለውና ሄዶ ከዳንስ ቤቱ ገባ፡፡
አባ ጳውሊም ከእርሱ ጋር ያለውን ዲያቆን ‹‹ወንድሜ
የዚህች አገር ሰዎች ኃጢአታቸው ታላቅ ነው››
አለው፡፡ ሌሊት በሆነም ጊዜ አባ ጳውሊ ቀስ ብሎ ተነሥቶ ማንም ሳያየው ወደዚያ የዝሙት ቤት እየጸለየ ሄደ፡፡ ከበርም ቆሞ ሰዎቹን ራቁታቸውን ሆነው ዝሙት ሲሠሩና ሲጮኹ ድምጻቸውን ሰማቸውና እጅግ አዘነ፣ አለቀሰም፡፡ ወደ ምድርም እየሰገደ ‹‹እነዚህ
ሰዎች ለሌሎች የኃጢአት ምሳሌ እንዳይሆኑ አጥፋቸው››
እያለ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማውና ሰዎቹን የሚያስታቸውን ሰይጣን ምሥጢሩን ይነግረው ዘንድ ሰይጣንን ወደ እርሱ ላከው፡፡ አባ ጳውሊም ጸሎቱን እንደጨረሰ ሰይጣን ጥቁር ሰው መስሎ እንደ እሳት የሚንቦገቦግ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ ራቁቱን ከዳንስ ቤቱ ሲወጣ አየው፡፡ ያም ሰይጣን በማስፈራራት ከዳንስ ቤቱ በር ላይ በቆመ ጊዜ አባ ጳውሊ ‹‹አንተ
ማነህ? ሰይፍህስ በእጅህ የተመዘዘው ለምድነው?›› አለው፡፡ ሰይጣኑም ‹‹የምትሻውን
ጠይቀኝ እንጂ አንተ ማነህ አትበለኝ! ከፈጣሪህ ከጌታህ የለምከውን አንተ ታውቃለህ፡፡ እኔ ከፈጣሪ ታዝዣለሁና የአዛዤን ትእዛዝ እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም››
አለው፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ‹‹ብዙ
ጥያቄ እጠይቅሃለሁና እንዳትዋሸኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም አምዬሃለሁ አውግዤሃለሁ››
ባለውና በመስቀሉም ባሰረው ጊዜ ሰይጣንም ‹‹የምትሻውን
ጠይቀኝ ትእዛዝህን አልተላለፍም፣ ኃይሌ በጸሎትህ ደክሟልና በፈጣሪም ስም አውግዘኸኛልና ሳልዋሽ እነግርሃለሁ››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹መጀመሪያው
ከሰዎች በአንዱ አድረህ በኃጢአት ትጥለው ዘንድ አጋዥ የሚሆንህ ምንድነው?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ‹‹ሰው
በእግዚአብሔር ሕግ ጸንቶ ሳለ በማንም ላይ ማደር አይቻለንም፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ ይቅር ባይ ከሆነ ከእግዚአብሔር ሕግ ትንሽ ፈቀቅ ቢል፣ እንዲሁም ደግሞ በየጊዜው ስሙን ባይጠራ ያንጊዜ በእርሱ ለማደር ኃይል እናገኛለን፡፡ የእግዚአብሔር ስሙን መጥራት ያልኩህም በፍጹም ሃይማኖት ሆኖ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ማለት ነው፡፡ ሕፃንም ቢሆን ከመጠመቁ በፊት እናቱ በላዩ ላይ የእግዚአብሔርን ስም የማትጠራና በመስቀል ምልክት በላዩ ላይ የማታማትብ ከሆነ እና እናድርባለን፡፡ ወላጆችና አሳዳጊዮች ይህንን መንፈሳዊ ሥራ ካልሠሩ በሕፃናት ላይ እናድራለን››
አለው፡፡
ዳግመኛም ሰይጣን ለአባ ጳውሊ እንዲህ አለው፡- ‹‹ሴትና
ወንድ ለመጋባት በወደዱና በፈቀዱ ጊዜ አስቀድመው በካህናት ጸሎትና በክርስቶስ ሥጋና ደም አንድ ከሆኑ ሥልጣን የለንም፡፡ ነገር ግን ከዚህ መንፈሳዊ ሥራ ቢርቁና በራሳቸው ፈቃድ ብቻ ቢጋቡ እኛ በእነርሱም ሆነ በልጆቻቸው ላይ እናድርባቸዋለን፣ አንሰለጥንባቸዋለን፡፡ ከዚያም ሰላምን አሳጥተናቸው ኑሮአቸው የጠብና የክርክር እንዲሆን በመጨረሻም መለያየት እንዲሆን እናደርጋለን››
አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሰው
ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ካልጸለየ እኛ የወደድነውን ሁሉ እናደርግበታለን፡፡ ዓለሙን ሁሉ ድል አድርገን እንገዛ ዘንድ ባለን ዐቅማችን እንታገላለን››
አለው፡፡
አባ ጳውሊም ቀጥሎ ‹‹የዓለምን
ሰዎች የምትፈትናቸው በምንድነው?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ‹‹እንደምኞታቸው
እንፈትናቸዋለን››
አለው፡፡ ቀጥሎም ‹‹እነርሱ ሊፈተኑ የሚችሉበትን ሥጋዊ ሀሳብን እናቀርብላቸዋለን፣ እናሳምርላቸዋለን፡፡ በኩራት በትምክህት እናቃጥላቸዋለን፡፡ እንቅልፍንና ዝሙት መመኘትን እናመጣባቸዋለን፡፡ ጾም እንዳይጾሙ፣ ጸሎት እንዳይጸልዩ እናደርጋቸዋለን፡፡ ከመልካም ሥራ ሁሉ እናርቃቸዋለን፡፡ ዘወትር ይህን ዓለም በማሰብ በስካር፣ በውሸት፣ በቂምና በቅናት፣ ሐሰት በመመስከር፣ ወርቅና ብርን በመውደድ፣ በስንፍና ሰውን በመሳደብ አእምሮአቸው እንዲጠፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱሳንን ሳይቀር የዘላለም ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንዲያጡ በተለያየ ምክንያት ባለን ኃይል ሁሉ እንዋጋቸዋለን፡፡ እኛ ኃይልና ሥልጣን የምናገኘው ፈጽመው ንስሓ በማይገቡ ሰዎች ላይ ነው፤ የሚጠብቋቸው ቅዱሳን መላእክት ስለበዳላቸው ሲርቋቸው ያንጊዜ እኛ በእነርሱ ላይ እንበረታለን››
አለው፡፡ ዳግመኛም ሰይጣን ለአባ ጳውሊ ‹‹እነዚህን
ሰዎች ክፉ ሥራን ሁሉ ወደው እንዲሠሩ እናደርጋቸዋለን፡፡ በዓለም ያለውን የክፋትና የድንቁርና ሥራዎች ሁሉ እንደ መልካም አስመስለን እናሳያቸዋለን፡፡ መልካም በማስመሰል በውሸት ሕልም እናስታቸዋለን፡፡ በዚህ ዓለም አኗኗር ከሰው ወገን እናጠፋው ዘንድ እኛ ሳንፈትነው ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይ የለም፡፡ እኛ እግዚአብሔርን መሳደብና መንቀፍ ባይቻለን ሰዎች ፈጣሪያቸውንና ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳን መላእክትን፣ ቅዱሳን ጻድቃንን ለመሳደብና ለመንቀፍ እንዲነሡ እናደርጋቸዋለን፡፡ ነገር ግን ንስሓ ገብተው ወደ ፈጣሪያቸው ቢመለሱና የክርስቶስን ሥጋና ደም ቢቀበሉ በነፍሳቸውም ንጹሐን ቢሆኑ እኛ በእነርሱ ላይ ፈጽሞ ኃይል የለንም››
አለው፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ‹‹ሰዎች
ነገርህን እንዴት አምነው ይቀበሉሃል? የመልክህን ክፋት የመዓዛህን ክርፋት አያውቁምን?›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህ ጊዜ ‹‹ሰዎች
ሁሉ እንደ አንተ መሰሉህ? በዚህ ዓለም መዓዛዬን ለማሽተትና መልኬን ለማየት እኔን የሚሹ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እነግርሃለሁ፡፡ እነርሱ ወደ እኔ መጥተው እገለጽላቸው ዘንድ ይለምኑኛል እንጂ እኔ ወደ እነርሱ አልሄድም፡፡ እኔን ለማየት በሚፈልጉት በመገለጽ አስደስታቸዋለሁ››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹መልክህን
መለወጥ እንደምን ይቻልሃል?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ይህ
የሚያስደንቅ አይደለም፣ ‹ሰይጣን
የብርሃን መልአክን መምሰል ይችላል›
ብሎ ጳውሎስ የተናገረውን አልሰማህምን?›› አለው፡፡አባ ጳውሊም ‹‹የማታውቀውን
ምሥጢር ማስመሰል እንደምን ይቻልሃል?›› ሲለው ዲያብሎስም ‹‹ዓለም
ከተፈጠረ ጀምሮ በዘመን ብዛት የሰበሰብኩት ብዙ ዕውቀት አለኝ፡፡ በዚህ ዓለም የማውቀው ብዙ ጥበብ አለኝ፡፡ ነገር ግን የክርስቶስ ሰው መሆን ብቻ ተሰወረብኝ እንጂ››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹የክርስቶስ
ሰው መሆን ስለምን ተሰወረብህ?›› ሲለው ዲያብሎስም ‹‹ከእኔ
የተሰወረበትን ምክንያት አላውቅም፡፡ አውቄስ ቢሆን ክፉና በጎ ለይተው ያላወቁ እልፍ ሕፃናትን በሄሮድስ አድሬ ባላስገደልኩ ነበር››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹ክርስቶስ
በእውነት አምላክ መሆኑን ያወከው መቼ ነው?›› ሲለው ‹‹በመስቀል
ላይ ተሰቅሎ ኃይሌን እስኪያደክመው ድረስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን አላወቅሁም ነበር››
አለው፡፡
አባ ጳውሊ ዳግመኛም ዲያብሎስን ‹‹ሰዎችን
በማሳሳትህ ምን ትጠቀማለህ?›› አለው፡፡ ዲብሎስም ሲመልስ ‹‹የእኔስ
ጥቅም የሰው ልጆችን ከዘላለም ሕይወት ማጥፋትና በገሃነም እሳት ማቃጠል ነው››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹በውኑ
ገሃነም የሚባል ቦታ አለን?›› ብሎ ሲጠይቀው ዲያብሎስም ‹‹አዎ
አለ እንጂ፡፡ በዚያ መጽናናት የሌለው ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት እንዲሁም ትሉ የማያንቀላፋ ነው፤ እኛም መኖሪያችን እዚያ ነው››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም መልሶ ‹‹አንተ
ከክብር የተዋረድክ በገሃነም እሳት እንደምትቀጣ ካወቅህ ለምን ንስሓ አትገባም? ብለው ጠየቁት፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ንስሓ
እንዳልገባ የሚጸጸት ልብ የለኝም››
አለው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹እግዚአብሔር
መሐሪና ይቅር ባይ ነውና ከለመንከው ይቅር ይልሃል››
አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ለዚህ
ሥራ ዕድል ፈንታ የለንም››
አለው፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ‹‹ለሰው በምትሐት የምትታዩት በስንት አምሳል ነው?›› ባሉት ጊዜ ዲያብሎስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፡- ‹‹ሰዎችን ለማሳት እኛ በምንፈልገው መልክ እርያ፣ እባብ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ቀበሮ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮና ሌላም መስለን መታየት እንችላለን፡፡ ከእኛ እያንዳንዳችን በድንግል ማርያምና በልጇ አምሳል በብርሃን መልክና በቀደሙ ቅዱሳን አምሳልም ቢሆን ሰው በሚፈልገው ሁሉ መስለን እንታያለን›› አለው፡፡ ////////////////////////////
ክፍል ሁለት
No comments:
Post a Comment