ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ (በምሥጢረ ሥጋዌ አስተምህሮ)

ክፍል ሁለት


         በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

   
 ይህም ምሳሌሲ ብራራ፡-
      * ከብታ ማለት ቤተ-ስብሐት ማለት ነው። ቤት የእመቤታችን ስብሐት የጌታችን። ኤፍራታ ማለት ጸዋሪተ ፍሬ (ፍሬ የምትሸከም፤ የሚዘይዝ) ማለት ነው። ጸዋሪት የእመቤታችን፤ ፍሬ የጌታችን ምሳሌ ነው።
        * ቤተ-ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ሲሆን ቤት የእመቤታችን ኅብስት (ልሔም) የጌታችን ምሳሌ ነው። ከቤተልሔም ኅብስት እንዲገኝ ከእመቤታችንም ለሰው ልጅ እውነተኛ ደሙንና ክቡር ሥጋውን የሰጠው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል።
       2አንቺ ቤተልሔምብሎ ስለቤተልሔም መገለጹ ስለማይቀር ቤተልሔምን አነሣ። ሌላኛው ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያው ምዕራፍ ትኩረት የተሰጠው ከጌታ መወለድ ጋር የሄሮድስ ስም አብሮ መነሳት ነው። ይኸውም፦
      * በጌታ መወለድ ምክንያት የተደናገጠው ሄሮድስ በቤተልሔም የሚገኙ ሕፃናትን መግደሉን ስለሚገልጽ ማቴዎስ ሄሮድስን አስቀድሞ ማስታወሱ ነው።
        * በእስራኤል ልምድ ትውልድ እና ዘመን የሚቆጠር በንጉሥ ነውና የሄሮድስን ስም አነሣ።
       * በንጉሥ ሄሮድስ ላይ ሰማያዎ ንጉሥ ተወለደ፤ እግዚአብሔር ክርስቶስ ተወለደ ለማለት ሄሮድስን አነሳው። በዚህም ከቤተ ይሁዳ ንግሥና አይጠፋም ተብሎ የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን ለማጠየቅ ነው። ከዚያው ከቤተልሔም ሳሉ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። የእንግዳ ማረፊያ ቢያጡ ከከብቶች በረት ዮሴፍ ዳስ ጥሎላት በሴቶች የሚደርሰው ሳይደርስባት ሕማመ ምጽ (የምጥ ሕማም) ሳይሰማት ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወልዳዋለች።እምሀበ አብ ወጽዓ ቃል ዘንበለ ድካም ወእም ድንግል ተወልደ ዘንበለ ሕማም፤ ከአብ ዘንድ ያለድካም ወጣ ከድንግልም ያለሕማም ተወለደእንዲል (ቅዱስ ኤፍሬም)

       ልደቱን ያለዘርዓ ብእሲ ያደረገው ለምንድን ነው? ቢሉ ቀዳማዊ ልደቱን ለመግለጽ ነው። ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለአባት መወለዱን ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያጠይቀናልና።ልደተ ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደት፤ የቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀእንዲል። አንድም የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድም ነው፡ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ፤ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለችተብሎ ተነግሯልና። (ኢሳ 714) ይህም አዳም ከኅቱም ምድር ተገኝቷል፤ ሔዋንም ከኅቱም ገቦ ተገኝታለች። ይህም ጌታ በኅቱም ማኅፀን ለመወለዱ ምሳሌ ነው።በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀእንዲል (ኢሳ 13) እንስሳት ጌታቸውን አውቀው እስትንፋሳቸውን ገብረውለታል። ቁረ ሌሊቱን ለመግለጽ ነው። በሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞች ነበሩ። መልአኩ መጥቶ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።አላቸው። (ሉቃ 210-12) ከሡም ጋራ ሠራዊተ መላእክት መጥተውስብሐት ለእግዚአብሔር በሠማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለእመሕያው፡ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ፤ የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር።” (ሉቃ 213-19)
         መላእክትም ሠማይ መንበሩ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆኑለት አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በጎል ተኝቶ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተውት ደስ ብሏቸው ወደሠማይ ቢያርጉ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በዕሪና ከመንበሩ አይተውትስብሐት ለእግዚአብሔር በሠማያትብለው አመስግነውት በጣዕም ላይ ጣዕም፤ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋል። ልደቱን ይሹታልና፤ መላእክትም ብቻ አይደሉም እንስሳትም አራዊትም ደስ ብሏቸዋል። ይህም ሊታወቅ አንድ ባሕታዊ ቋርፍ ሲምስ ምዳቋ ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም ዮም ተወልደ ከሣቴ ብርሃን እያለች ስትዘል አይቷል። በልደቱም የባሕር ውኃ ወተትና ማር ተራሮች እንጀራ እንጨቶችም የበረከት ፍሬ ሆነዋል።በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ.ሕይወት ወዕፀ.ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት ማየ.ባህርኒ ሞነት ሐሊበ ወመዓረእንዲል ቅዱስ ያሬድ።
        ልደቱንም በኮከብ ተረድተው ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ስማቸውም ማንቱሲማር፣ ሜልኩ በዲዳስፋ የተባሉ የፋርስ ነገሥታት ከገነት የተገኘ ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ገብረውለታል። ከምን አገኙት? ቢሉ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ሰጡት። እርሱ ለሔዋን ሰጣት። ሔዋን ለሴት ሰጠችው። ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደረሰ። ኖኅ ከመርከብ ከወጣ በኋላ ለሴም ሰጠው። ሴም መልከጼዴቅን አስጠበቀው፤ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ሰጠው። ከአብርሃም ሲወርድ ሲዋረድ በዳዊት በሰሎሞን አድርጎ ከአካዝ ደረሰ። በሱ ዘመን ቴልጌልፌልሶር ማርኮ ወስዶ ከቤተ.መዛግብቱ አኑሮታል። አባታቸው ዥረደሽት ይባላል፤ ፈላስፋ ነበር። አንድ ቀን በቀትር ከውኃ ዳር ሆኖ ሲላሰፍ በሰሌዳ ኮከብ ድንግል ሕፃን ታቅፋ አየ። ያየውን በሰሌዳ ቀርጾ አስቀመጠው። ሲሞት ልጆቼ እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ይህን ወስዳችሁ እጅ ንሱ ብሎ ሰጥቷቸዋል። አንድም በለዓምከያዕቆብ ቤት ኮከብ ይወጣልያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። (ዘኅ 2017) አንድም ትሩፋን በባቢሎን ሳሉ ነገሥተ ተርሴስ ወደ ስያት ስጦታ (ገጸ በረከት) አመጡ፤ ንግሥተ ሳባ ወዓረብ እጅ መንሻ ያመጣሉ እያሉ ሲጸልዩ ይሰሙ ነበረና ይኸን ይዘው መጥተዋል። አንድም ባሮክ አቴና ወርዶ ነበር። ያን ጊዜ ዛሬ የሀገራችሁን ንጉሥ የሚገብረውን ወርቅ ኋላ ከእኛ ወገን ንጉሥ ሲወለድ ይገብረዋል ብሎ የነገራቸውን ይዘው ነው።
        የተወለደ ዕለት ኮከቡን አይተው አባታችን የነገረን ደረሰ ብለው 12 ሆነው ሠራዊቶቻቸውን አስከትለው ተነሱ። ብዙም ሳይርቁ ጠላት ተነስቶባቸው ዘጠኙ ተመለሱ። እኒህ ሦስቱ ግን ኮከቡ እየመራቸው ኢየሩሳሌም ደርሰው በሄሮድስ በኩል አድርገው ቤተልሔም ወርደው አግኝተው ገብረውለታል። ምሥጢሩም፡-
       ፩፦ ወርቅ መገበራቸው፡ ይኸን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ነህ፤ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ እንዲሁም በአንተ ያመኑ ምዕመናንም ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው። የሃይማኖት ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና።
፪፦ ዕጣን መገበራቸው፡ ይኸንን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። አንድም ዕጣን ምዑዝ ነው፤ አንተም በባሕርይ ምዑዝ ነህ ሲሉ እንዲሁ ደግሞ በአንተም የሚያምኑ ምእመናንን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ዕጣን የተስፋ ምሳሌ ነው። ዕጣን ከሩቅእንዲሸት ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና።
       ፫፦ ከርቤ መገበራቸው ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ በኋላም የማታልፍ ብትሆንም በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ አንድም ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ። አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት። ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው። በፍቅር አንድ ይሆናሉና። ከርቤ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ አንድ እንዲያደርግ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና። በአጠቃላይ ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ እጣን ከርቤ የገበሩለት ሃይማኖት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ነው። በሌላ መልኩ ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለመለኮቱ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ ናቸው።
       እጅ ነስተው ከወጡ በኋላ አንዱ እንዴት ያለ ሽማግሌ ነው ብሎ አደነቀ። ሁለተኛው የምን ሽማግሌ ጎልማሳ ነው እንጅ አለ። ሦስተኛው ደግሞ ሕፃን ነው እንጂ አለ። ገብተን እንይ ተባብለው ቢገቡ ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ፤ ጎልማሳ መለስሎ ለታየው ሕፃን፤ ሕፃነ መስሎ ለታየው ሽማግሌ መስሎ ታያቸው። ወጥተው እንዳንተ ነው እንዳንተ ነው ይባባሉ ጀመር። መልአኩ መጥቶ እንደሁላችሁም ነው አላቸው። በጆሮ የሰሙትን በዓይን ቢያዩት ይረዳል ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ገቡ። ሽማግሌ ጎልማሳ መስሎ ለታየው ሕፃን፤ ጎልማሳ ሕፃን መስሎ ለታየው ሽማግሌ፤ ሕፃን ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ መስሎ ታያቸው። እጹብ እጹብ ብለው አመስግነው፤ አምላክነቱን ተረድተዋል። በሚሄዱበትም ጊዜ እመቤታችን የገብስ እንጀራ ጋግራ ሰጠቻቸው። ሀገራቸው እስኪገቡ ድረስ ከሠራዊቶታቸው ጋር (እያንዳንዳቸው አስር ሺህ፤ አስር ሺህ ሠራዊት) ሲመገቡ ቆይተው ከከተማቸው ሲደርሱ ይህን ቅዱስ ምግብ ከከተማችን አናስገባም ብለው ከከተማው በር ቀብረውት ገቡ። ደርሳችሁ መጣችሁን? አሏቸው። አዎን በአርባ ቀን መጣነው፤ እናቱም የሰጠችንን የገብስ እንጀራ እኛ እና ሠራዊቶቻችን ስንመገበው መጥተን ከከተማችን አናገባም ብለን ከከተማው በር ቀብረነዋል አሏቸው። አሳዩን አሉ። ተያይዘው ቢሄዱ ሲጨስ አግኝተውታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወድንግል ማርያም!
መልካም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ይሁንልን!!!
---------------------------- // -----------------------------
ምንጭ፦ [የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ //ቤት፤ መንፈሳዊ ድረ ገጽ]


No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ