ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ (በምሥጢረ ሥጋዌ አስተምህሮ)
ተሠገወ፡- ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ “ሥጋዌ” ሰው መሆንን፣ መገለጽን (በተአቅቦ)፣ መግዘፍን፣ መወሰንን፣ መዳሰስን ያመለክታል። ቀድሞ ምን ነበር? ወይም ማን? ለሚለው ጥያቄ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል “በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ.1፥1) ሰው የሆነም አካላዊ ቃል እንደሆነ “ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ም ተመልቶ በእኛ አደረ።” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐ.1፥14) ሰው የሆነውም በተዋሕዶ ነው። ይኸውም “አንድ ጊዜ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው” በማለት ነው። ምሥጢረ ሥጋዌ የአብ አካላዊ ቃል ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል ሰው የሆነበት፤ ሰውንም ያዳነበት መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ማለት ነው።
ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) የለም። ሞትን በቀመሰ ጊዜም መለኮት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም። በዚህም ምክንያት ሞቱ እንደሌሎች ፍጡራን ወይም እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የማይታይ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ “እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፤ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።” ሲል ገልጦልናል። (ዕብ. 2፥14) በመሆኑም ሲራብም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲተኛም፣ ሲነሳም፣ ተዓምራት ሲያደርግም፤ በአንድ ባሕርይ ጸንቶ እንጂ እንደ ማየ ግብጽ በሚጠት አንድ ጊዜ አምላክ አንድ ጊዜ ሰው እየሆነ አይደለም።
ሰው የሆነውም እንደ ወይነ ቃና እና እንደ ብእሲተ ሎጥ (የሎጥ ሚስት) በውላጤ (በመለወጥ) እንደ መስኖ ውኃ በኅድረት፤ ሳይሆን ተአቅቦ ባልተለየው ተዋሕዶ ነው። “የሰውን ሥጋ ነሥቶ ቢዋሐድ እንጂ ሥጋንማ ባይነሳ እንደምን ሰው በሆነ ነበር፤ ነፍስን ሥጋን መዋሐዱም መለወጥ፤ መቀላቀል ፤መለየት በሌለበት የሁለቱን ባሕርያት አንድነት እነደፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ አንድ አደረገ። ሥጋ ሥጋ ነውና፤ መለኮት አይደለም። እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ቢሆንም ቃልስ አሁን አምላክ ነው። ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም። ሥጋን ለራሱ ገንዘብ ቢያደርግም፤ በዚህም ደግሞ ከተዋሕዶ በምንም በምን አይናወጥም። ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል ፤ አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም። መከፈል የሌለበትን አንዱን ሁለት እናደርገው ዘንድ አንከፍለውም። አንድ ወልድ አንድ ባሕርይ ነው ብለው እንደተናገሩት። ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር በልቡናችን እንደምናውቅ በነፍሳችን ዓይንም እንደምናይ መጠን ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋልና አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ገዢ፣ አንድ ወልድ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ እግዚአብሔር ቃል ነው እንላለን።
“የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ሲያስብ፤ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው እንዲህም አለ፡- የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ እነሆ ድንግል ተፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል። የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይሁ ሁሉ ሆኗል። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ። እጮኛውን ማርያምን ወሰደ። የበኵር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም። ስሙንም ኢየሱስ አለው።” (ማቴ 1፥18-25) ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችንን ልደት ለመናገር አስቀድሞ የተናገረው ጽንሰቱን ነው። ፅንሰት ልደትን ይቀድማልና። ስለፅንሱ ሲናገር ደግሞ እመቤታችን ጌታችንን የፀነሰችበትን ጊዜ በቤተ ዮሴፍ ሳለች መሆኑን ጨምሮ በመግለጽ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ ስለፅንሰቱ ሁለት ነገሮችን ብቻ መግለጽ እንደተቻለው ለመረዳት ይቻላል።
አንደኛው፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ (እንዲጠብቃት፤ እንዲላካት፤ እንዲያገለግላት) የነበረች መሆኑን። ይህም ጥበብ የእግዚአብሔር ነውለ ፅንሱ ከመጀመሪያው በድንግልና መሆኑ ታውቆ ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ጌታን ያገኘ መስሎት ብዙ ፅንስ ሊያስወርድ ይችል ነበር። ምክንያቱም በኋላ ሰብአሰገል ሁለት ዓመት እንደተጓዙ ሲነግሩት፤ ከሁለት ዓመት በታች ያሉትን ሕፃናት በሄሮድስ አድሮ አስጨፍጭፏልና።
ሁለተኛ፡- ቅዱስ ማቴዎስ ስለጌታችን ፅንስ የተናገረው ሌላው ዐቢይ ነገር ከዮሴፍ ጋር አለመገናኘቷን ብቻ ሳይሆን በግብረ መንፈስቅዱስ ፀንሳ መገኘቷን ብቻ ነው። እንዴት ሆና? ለሚለው ግን መልስ ሊሰጥ አልሞከረም፤ አይቻልምና። እንኳን እርሱ ቅዱስ ገብርኤልም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይል ይጸልልሻል። ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” አላት እንጂ እንዴት እንደሚከናወን መረዳት አልተቻለውም። (ሉቃ 1፥35) ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ውጤቱን ወይም ክንውኑን እንጂ አሠራሩን የምንረዳበት ዐቅም የለንምና ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የማይወሰነው (የሚወስነው ዓለም የሌለው) እርሱ በማሕፀንሽ እንዴት ተወሰነ? ዓለሙንም የያዘ እርሱ እንዴት በማሕፀንሽ ተሸከምሽው? በድንግልና ተፀንሶ ድንግልናዋ አለመለወጡስ እንደምን ያለ ነው? በማሕፀን ሲዋሐድስ ሥጋዋን ሁሉ እንደምን አልነሳም? እንዴትስ እርሱን አሳደገ? እርሱንስ እንዴት ተዋሐደ? እርሱ ከድንግል በፊት ነበርና።” እያለ ሊመረምርና ሊነገር በማይቻል ባሕርዩን በመደነቅ ይገልጻል።
ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችንን የተቀበለው ሊጠብቃት፣ ሊንከባከባት እንጂ ሚስት ትሆነው ዘንድ አይደለም። ይኸንም ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ገልጾታል። የዮሴፍም ጽድቅ የተገለጠው በዚሁ ምክንያት ነው። ምክንያቱም ለሚስትነት ወስዷት ቢሆን ኖሮ ከእርሱ እንዳልፀነሰች እያወቀ እርግዝናዋን ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም ነበር። እንኳን በግብር ሳያውቃት ቀርቶ በግብር ቢያውቃትም ፅንሱ ከእርሱ እንዳልሆነ ከጠረጠረ (በባልና በሚስት መካከል መቀናናት በተከሰተ ጊዜ፥ "የቅንዓት ሕግ" በተባለው መሠረት) በኦሪቱ ሥርዓት መሠረት ወደ ሊቃነ ካህናቱ ይወስዳታል፤ ጥርጣሪውንም ይናገራል። ካህኑም ወንዱ ይዞት የመጣውን የገብስ ዱቄትና ውኃ በቤተ መቅደሱ ካለ የዕጣኑ ዕራፊ ጋር ቀላቅሎ የሚጸልየውን ጸልዮ “ ባልሽ የጠረጠረሽን አድርገሽው ከሆነ፤ ሥጋሽ ይበጥ፣ ቁርበትሽ (ቆዳሽ) ይላጥ፤ አላደረግሽው እንደሆነ በወንድ ልጅ ተበከሪ” ብሎ ይሰጣታል። እርሷም መርገሙ ይደረግብኝ በረከቱ ይሁንልኝ ብላ ትጠጣዋለች። (ዘኍ 5፥11-31) ዮሴፍ ግን ይኸን በሕግ የተፈቀደውን ያላደረገው መጀመሪያውኑ ሊጠብቃት፤ ሊያገለግላት የተቀበላት በመሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ ዮሴፍ ጭንቀት አልቀረለትም። ከመጨነቁም የተነሳ ከሁለት ነገሮች በአንዱ ላይ መወሰን ተስኖት በአሳብ ይዋዥቅ ነበር። ወደቆጠራው ይዟት እንዳይወጣ “ልትጠብቃት ሰጥተንህ ለምን እንዲህ አደረግህ?” ተብሎ ቢጠየቅና የእርሱ አለመሆኑን ቢናገር እርሷን እንደ ሕጋቸው በድንጋይ ወግረው፣ በእሳት አቃጥለው ይገድሉብኛል ብሎ ተጨነቀ። ትቷት ቢሄድም ያደረገውን ዐውቆ ወደ ቆጠራ ሳይዛት መጣ የሚሉ ከሳሾችን ፈራ። በእነዚህ በሁለቱ ሲጨነቅ፣ ሲያወጣ ሲያወርድ፣ ሲፈራ ሲቸር መልአኩ በሕልም አነጋገረው። ወንጌላዊው “እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።” ያለው ይኸንኑ ለመግለጥ ነው።
የዮሴፍም ጽድቅ የወንጌል እንጂ የኦሪት አይደለም። ዮሱፍ ግን በግብር ፈጽሞ ስለማያውቃት ሆኖ ሳለ እንኳ ሊተዋት ነገሩን ላገልጥባት አስቧልና። ይኸም በወንጌል ያለ፤ ከባቴ አበሳነት ነው። ስለዚህ ዮሴፍ ጻድቀ ወንጌል እንጂ ጻድቀ ኦሪት አይባልም። ዮሴፍ በዚህ ግብሩ ጻድቅ ቢሆንም ለቆጠራው የሚያደርገው አስጨንቆት ነበር። መልአኩ በሕልም ተገልጦ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።” ያለውም ለዚህ ነው።
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከመናገሩ በፊት በሥጋ ብእሲ መገለጡን ለማስረዳት ከአብርሃም በመነሳት የሌሎቹን ልደት እየተናገረ መጥቷል። ስለልደታቸው ሲገርም ፍፁም ዕሩቅ ብእሲ መሆናቸውን በመግለጥ ነው። ይኸውም “አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤…” በሚለው አገላለጽ ነበር። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ እናታቸውንም ይገልጻል። “ንጉሥ ዳዊት ከኦርዮን ሚስት ሰሎሞንን ወለደ” እንዳለ። ልደተ.እግዚእን ሲገልጽ፦ “ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናል እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።” (ማቴ. 2፡1) አለ። ቅዱስ ማቴዎስ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሲገልጽ በቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን መወለዱን አውስቷል። የቤተልሔምንና የሄሮድስን ስም ለምን ማንሳት አስፈለገው? ቢሉ፦
1፦ የተናገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ ለመከተል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ስለ ጌታ መወለድ የጻፈው በነቢያት ስለቤተልሔም የተነገረውን ትንቢትና በኦሪት የተመሰለውን ምሳሌ በማስታወስ ነው። ትንቢቱም “ወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉሥ ዘይርእዮም ለሕዝብየ እስራኤል፤ አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና።” የሚል ነው። ምሳሌው ደግሞ ካሌብ ምድረ ርስትን ሰልሎ ሲመለስ ኬብሮንን አይቶ መጥቶ ኢያሱን ኬብሮንን ስጠኝ ቀድሞ ሙሴ ሰጥቶኝ ነበር። (ሚክ 5፥2) ምንም እንኳን የ80 ዓመት ሽማግሌ ብሆንም ከአንተ ጋር መውጣት መውረድ የሚያስችለኝ ጉልበት አለኝ። ብሎ ከኢያሱ ኬብሮንን ወሰደ። እርሷን እጅ አድርጎ አዙባ የምትባል ሴት አገባ። ከጠላቶቹ ወገን ነበረችና በእርሷ ስም አልጠራትም። ቀጥሎ ከብታ የምትባል አገባ፤ በከብታ ከብታ ተባለች። እንደገናም ኤፍራታ የምትባልም ሲያገባ ኤፍራታ ተባለች። ካሌብ ወንድ ልጅ ከሷ በወለደ ጊዜ እንጀራ እገባ እገባ ብሎት ስለነበር (ሀብት ስላገኘ) የልጁን ስም ልሔም (ኅብስት) አለው። በልሔም ቤተ-ልሔም ተብላለች።... ክፍል ሁለት
ምንጭ፦ [የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ሰ/ት/ቤት፤ መንፈሳዊ ድረ ገጽ]

No comments:
Post a Comment