ኅዳር 21 የሚከበረውን የእመቤታችን በዓል በማድረግ ስለ ታቦተ ጽዮን አሰራርና ምሳሌነት እንዲሁም ስለ ታቦትና ከሀዲዎች ከሁለት መጻህፍት ምንጭ በማድረግ ቃል በቃል የሰፈረ
በዲ/ን አውራሪስ በላይ
‟"እኛን ክርስቲያኖች መስለው የገቡ አባታቸው ዲያቢሎስም ካነቀው ስህተት አይርቁም እኛ ግን በእግዚአብሔር ታቦተ ህግ በፅዮን ውስጥ እንስግድ ዘንድ ይገባል፡፡ መጀመሪያዋም እሷ ናት ዛሬም አሁንም እሷ ናት ምሳሌዋም ፍሬዋም የመድሃኒታችን እናት ማርያም ናት፡፡ እንስግድላት ዘንድ የእግዚአብሔር ታቦተ ህግ በእሷ ስም ተባርካለች፡፡" ክብረ ነገሥት
❖የበዓሉ ምክንያት፡-
✍ታቦተ ጽዮን በአምስቱ የፍልስጤም ከተሞች ተዓምራቷን ገልጻ ከ20 ዓመታት በኋላ በድል አድራጊነት ወደ እስራኤል የገባችበት፡፡ 1ኛሳሙ ምዕ5- 6፤
✍ ታቦተ ጽዮን የፍልስጤማዊያንን ጣኦት ዳጎንን ያፈራረሰችበት፡፡ 1ኛሳሙ ምዕ5 ፤
✍ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ አዜብ ሳባ ወደ ፍልስጤም በመሄድ የሰሎምንን ጥበብ ማድነቋና በልጇ በእምነ መለክ (ቀዳማዊ ምኒልክ) አማካኝነት ከሌዋዉያን ካህናት ጋር በመሆን ታቦተ ጽዮን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገባችበት፤ 1ኛነገ 10፡ 1-13፤ 2ኛዜና መዋዕል 9፡1-12
✍ ስለ ታቦት ክብር በስፋት የሚገለጥበት
✍ በሀገራችን በአክሱም የመጀመሪዋ ቤተክርስቲያን አክሱም ጽዮን የታነጸችበት በዓል ነው፡፡
❖ የቃል ኪዳን ታቦት ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ክፍል አንድ
የአምላክ ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በልዑል እግዚአብሔር ትእዛዝ ጥበብና ማስተዋል በተሰጠው በባስልኤል እጅ በተሰራችው የቃል ኪዳን ታቦት ትምስላለች ይኽቺ ም ፦
✿ የእግዚአብሔር የጌትነቱ መግለጫ የኾነችው
✿ በፍልስጥኤም ይምለክ የነበረ ጣዖትን ቀጥቅጣ ያጠፋች፤
✿ በድፍረት ሊነካት የሞከረ ኦዛን የቀሰፈች፤
✿ በታላቅ ክብር ወደ ሀገሯ ስትመለስ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በታላቀ መንፈሳዊ ደስታ በፊቷ የዘመረላት ፤
✿ ልጁ ሰሎሞንም ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቶ በክብር ያኖራት ናት፡፡
ጌታ የታቦቷን አሠራር ሲነግረው ሽምሽር ስጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት ቀርጸኽ አብጅ ከታች እንደ ዙፋን አራት እግር አውጣለት ሞላልነቱን ኹለት ክንድ ከስንዝር ቁመቱ ክንድ ከስንዝር ወርዱን ክንድ ከስንዝር ኹለት ክንድ ከስንዝር ምስሃል ለዚኽ ቁመት የለውም አራት ቀለበት ኹለት ሙሎጊያ አበጅለት አፍአውን ውስጡን በንጹሕ ወርቅ ለብጠው በምስማኩና በምስማኩ ኹለቱን ኪሩቤል እንደሚናተፉ አወራ ዶሮዎች አንገታቸውን ደፋ አድርገኽ አድርገኽ በላይ ሣልበት ዙሪያውን ፈለግ አውጣለት ብጽብጽ ወርቅ አፍስበት ጽላቶቹን በውስጡ አኑር ብሎታል፡፡
ይኸውም ምሳሌ
✔ታቦት ፡- የእመቤታችን
✔ ወርቅ፡- የንጽሕናዋ የቅድስናዋ
✔ ታቹ መቀመጫው ፡- የንጽሓት እንስት
✔ ላዩ መግጠሚያው ፡- የንጹሓን አበው
✔ ግራ ቀኙ ፡- የሐና የኢያቄም
✔ ወደ ውስጥ የገባችው ፡- የድንግል ማርያም ያቺ በመኻከላቸወም እንደኾነች እመቤታችንም ከሐና ከኤያቂም ለመገኘቷ ምሳሌ ነው
✔ኹለት ክንድ ከስንዝር፡- ከአዳም እስከ ኖኅ ባለው ዘመን 2260 ዘመን ይመስላል ይኸውም በኖኅ ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ኖኅ ለመገኘቷ ምሳሌ፡፡
✔አንድ ክንድ ከስንዝር ቁመቱ ፡- ከኖኅ እስከ ሙሴ ባለው ዘመን ይመስላል ይኸውም 1600 ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን አርአያ ድንግል ጸላተ ሙሴ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው፡፡
✔ አንድ ክንድ ከስንዝር ወርዱ፡- ከሙሴ እስከ እመቤታችን ባለው ዘመን ይመስላል ይኽውም 1640 ዘመን ይኾናል ይኽ በኾነ አርአያ ድንግል ታቦተ ኖኅ አርአያ ድንግል ጽላተ ሙሴ ምሳሌዎቿ የሚሆኑ አማናዊት ድንግል ማርያም ለመገኘቷ ምሳሌ ነው፡፡
✔ አራቱ ቀለበት፡- የአራት ወገን ንጽሕናዋ ምሳሌ ይኸውም ክርእይ /ኃጢአትን ከማየት/፤ ከሰሚዕ/ኃጢአትን ከመስማት/ ፤ ከገሲስ/በእጅ ዳሰሶ ኃጢአትን ከመሥራት እና ከአጼንዎ /የኃጢአትት መዐዛን ከማሽተት/ እመቤታችን ከነዚኽ ኹሉ ተጠብቃለችና
✔ ኹለቱ ቀለበት፡- የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌ
✔ ኹለቱ ሥዕለ ኪሩቤል፡- የጠባቂ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልና የአብሳሪ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ምሳሌ ናቸው ይኽውም የብሉይ ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ቀን ገብቶ ከኹለቱ ኪሩቤል መኻከል ቃል ሰምቶ ይወጣ ነበር ቅድስት ድንግል ማርያም በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ተጠብቃ ከቅዱስ ገብርኤል ቃል ሰምታ አካላዊ ቃልን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ ፀንሳ ተገኝታለችና
ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ይኽንን መንፈሳዊ ምስጢር በጥልቅት በመመርመር ድንግል ማርያምን ፡-
➊በምስጢር የተመላች ታቦት
➋ እሳትን የተመላች ታቦት
➌ የቅዱስ ቃል ታቦት
➍ የቃል ኪዳን ታቦት በማለት ገልጿታል፡፡
❖ስለ ታቦት ና ከሃዲዎች ነገር ከክብረ ነገሥት መጽሐፍ
➊ ስለ ታቦት ግን ኖህን በመርከብ አዳነው፡፡ አብርሃምን በማይነቅዝ የመንበሩ እንጨት ስር አናገረው፡፡ ይስሐቅንም በሐረግ-ሬሳ(ዕፀ-ሳቤቅ) በተያዘ በግ ታደገው ያእቆብንም በውሃ ውስጥ በጨመራቸው ሶስት የእንጨት ብትሮች ሀብታም አደረገው፡፡
➋ ዮሴፍም በያእቆብ በትር ጫፍ ተባረከ፡፡ ሙሴን በቃል ኪዳኑ ታቦት በፅዮን አምሳል ከማይነቅዝ እንጨት ታቦትን ስራ አለው፡፡ ዳዊት ታቦተ ህግን ከሰማርያ ሲወስዳት በአዲስ ታቦት ውስጥ አስቀመጣት በፊቷም ተደሰተ ታቦትን ከጥንት ጀምሮ መድሃኒት አድርጓታልና፡፡ በብዙ አርአያና ምሳሌ ብዙ ተአምርና ድንቅ ነገር ተደርጎባታልና፡፡
➌ አስረድቼ እገልጽላችኋለሁና ስሙኝ እግዚአብሔር መድሃኒትን በዕፅ መስቀሉና በታቦተ ህጉም ውስጥ እንዳደረገ የአዳምም ድህነት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእንጨት ሆነ፡፡
➍ የመጀመሪያው ስህተቱ በእንጨት ነውና ድህነቱን ከድሮ ጀምሮ በእንጨት አደረገለት፡፡ እሱ ራሱ ጌታ ፈጣሪ ህይወትና ሞትም ሰጪ ነውና ሁሉ በቃሉ ይደረጋል ሁሉን እሱ ፈጠረ
➎ ንፅህት በሆነችው በታቦተ ህግም ውስጥ በንፁህ የሚገዛውን ሁሉ ያፀድቀዋል፡፡ መማለጃ ተብላለችና ሞግዚት ተባለች፤ መስዊያም ተባለች ፤የሃጢአት ማስተስረያም ተባለች፤ የመጠጊያ አገርም ተባለች፤ መርከብ ተባለች ፤የድህነት ድልድይ ተባለች ፤ቤተ ጸሎት ተባለች፤ ስጋቸዉንም እንዳያረክሱ በንፁህ ይለምኑት ዘንድ በእሷ በንፁህ ለሚለምኑት የኃጢአት ማስተሰሪያ ሆነች፡፡
➏ እግዚአብሔር ንፁሁን ይወዳልና ወደ ቤቱ ለሚገቡና በቅድስት ታቦት ለሚያዙ በሙሉ ልባቸውም ወደ እሱ ለሚጸልዩና ለንፁሆች ማደሪያ ነው፡፡ እሱም በችግራቸውም ቀን ይሰማቸዋል ያድናቸዋልም፡፡ ፈቃዳቸውንም ያደርጋል የተቀደሰችውንም ታቦት በመንበሩ አስምስሎ ሰርቷታልና፡፡
➐ እኛን ክርስቲያኖች መስለው የገቡ አባታቸው ዲያቢሎስም ካነቀው ስህተት አይርቁም እኛ ግን በእግዚአብሔር ታቦተ ህግ በፅዮን ውስጥ እንስግድ ዘንድ ይገባል፡፡ መጀመሪያዋም እሷ ናት ዛሬም አሁንም እሷ ናት ምሳሌዋም ፍሬዋም የመድሃኒታችን እናት ማርያም ናት፡፡ እንስግድላት ዘንድ የእግዚአብሔር ታቦተ ህግ በእሷ ስም ተባርካለች፡፡
❖❖ከእመቤታችን በረከት ከታቦተ ጽዮን ፍቅር አይለየን❖❖


No comments:
Post a Comment