ሰይጣን በአባ ጳውሊ ተገዝቶ ሳለ ያወጣው ምሥጢር


 ክፍል ሁለት 

ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ‹‹ሰዎች ፈጣሪያቸውን እንዲክዱ የምታደርገው በምን መንገድ ነው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ነዚህ ዓለም የማደርገውን ሁሉ ነገርኩህ፤ መጀመሪያ ልጆች የወላጆቻቸውንና የአሳዳጊዎቻቸውን ምክር እንዳይሰሙ ለቃላቸውም እንዳይታዘዙና ‹እናንተ ይልቅ በእውቀት እኛ እንበልጣለን፣ እኛ እናውቃለን› እንዲሉ እናደርጋቸዋለን፡፡ ዳግመኛም ወላጆቻቸውንና በዕድሜ የሚበልጧቸውን እንዲሳደቡ እናደርጋቸዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት የቤተሰብ ፍቅር እናሳጣቸዋለን፡፡ በየሄዱበት ሁሉ እንደተረገሙ ይኖራሉ፡፡ ከዚህም በኋላ በክህደት፣ በዝሙት፣ የምንዝር ጌጥን በመውደድ፣ በስካር፣ በስርቆት፣ ነፍስን በመግደል ፈጽመው እንዲወድቁ እናደርጋቸዋለን፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ቆርጠውና አእምሮአቸውን አጥተው ቁጥር የሌለው ኃጢአትን እንዲሠሩ እናደርጋቸዋለን›› አለው፡፡
ዳግመኛም አባ ጳውሊ ‹‹እናንተ አሳቾች እንደሆናችሁ ለሰው በምን ትታወቃላችሁ? መጨረሻችሁስ እንዴት ነው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹እንደ አንተ ንጹሕ የሆነ ሁሉ በሥራዬ ያውቀኛል፤ ኃጥአን ግን ሽታዬን ለይተው ሊያውቁኝ አይችሉም፡፡ ለጥቂት ደጋጎች ነው እንጂ ለሁሉ አንታወቅም፣ በመጨረሻ ሥራችን ግን እንተወቃለን›› አለው፡፡
አባ ጳውሊም ‹‹በዕድሜ ያረጀ ዘመኑም የተቃረበና ሥጋውም የደከመን ሽማግሌ በምን ትፈትኑታላችሁ?›› ብሎ ሲይቀው ዲያብሎስም ‹‹እኛ በሽማግሌዎች ብዙ ምክንያት እናገኛለን፡፡ ስንፍና እናመጣባቸዋለን፡፡ ጾም ጸሎትን እንከለክላቸዋለን፡፡ ዘመናቸውን እስኪረግሙና ራሳቸውን እስኪያጠፉ ድረስ የሚያደርስ ጥርጣሬን እናመጣባቸዋለን፡፡ ክፉ ሀሳብና ገንዘብ መውደድን፣ ሰላም ማጣትን፣ ተስፋ መቁረጥን በውስጣቸው እናደርጋለን፡፡ ከልባቸው የሕሊና ጸሎትን ከአንደበታቸው ምስጋናን እናጠፋባቸዋለን›› አለው፡፡

ቀጥሎም አባ ጳውሊ ‹‹እንዴት አድርገው ነው በገዳም ከሚኖሩት ጋር የምትዋጋው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹አስቀድመን መነኮሳትን የምንዋጋው በገዳሙ ቆይታ ላላቸው ትላልቅ አባቶች እንዳይታዘዙ ለማኅበሩ አባት እሽ በጄ ብለው ምክራቸውን እንዳይሰሙ እናደርጋቸዋለን፡፡ እኔ የምነግራቸውንና የማሳስባቸውን ለአበው እንዳይነግሩ በማድረግ ነው፡፡ ዳግመኛም ጥርጣሬን እናመጣባቸዋለን፡፡ በሐሰተኛ ሕልም እናስታቸዋለን፡፡ በዚህ ባያምኑና ቢያሸንፉን ሌላ ብዙ የምኞት ፈተና እናመጣባቸዋለን፡፡ ገንዘብ መውደድን፣ የላመ የጣፈጠ መብላት መጠጣትን እናስመኛቸዋለን፡፡ ያለምክንያት በየጊዜው ሴቶች ወንዶችን ወንዶችም ሴቶችን እንዲያዩና እንዲገናኙ እናደርጋቸዋለን፡፡ በዚህም በእነርሱ ላይ ታላቅ ውድቀትና አእምሮ ማጣትን እናመጣባቸዋለን፡፡ የማይጠቅም ዙረትን እንዲያበዙ እናደርጋቸዋለን፡፡ ሰውን የሚያጣሉና ነገር አመላላሾች እንዲሆኑ የአባቶችን ምክር እንዳይሰሙ፣ ሥራን እንዳይወዱ በአኗኗራቸው በአንድ ቦታ እንዳይጸኑ እናደርጋቸዋለን፡፡ በአፋቸው ‹እኛ ዓለምን ንቀናል› እንዲሉ ነገር ግን የዓለም ፍላጎታቸው በላያቸው በዝታ እንዲትታይና መንፈሳዊ ዕውቀትን ትዕግስት መረጋጋትን እንዲያጡ እናደርጋለን፡፡ ከገዳማቸው በወጡ ጊዜ ከገዳማቸው ልቡናቸውን እናርቃለን፣ እኛ የዚህን ዓልም ሥራ ስለምናሳምርላቸው በስም መነኮሳት ሲባሉ በገዳም መኖራቸውን ፈጽመው ይጠላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ፈትነናቸው ቢያሸንፉን ሌላ የሚፈተኑበትን መንገድ እናመጣባቸዋለን፣ ሌላው በሚሠራው ሥራ በቅናትና በቂም እንዲነሡና ሌላውን እንዳይሠራ እንዲያውኩት እናደርጋቸዋለን፡፡ በመሠሩት በማንኛውም ሥረራ ውዳሴ ከንቱን እንዲፈልጉና ራሳቸውን ክፍ ከፍ እንዲያደርጉ ሌላውንም እንዲነቅፉ እናደርጋቸዋለን›› አለው፡፡
አባ ጳውሊም ‹‹በዚህ በምታመጣባቸው መከራ ምን ትጠቀማለህ? እነርሱስ በምን ያሸንፉሃል?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ፈጣሪያቸውን እንዳያመሰግኑና ተስፋ እንዲቆርጡ ከዘላለም ሕይወት እንድናቸጠፋቸው እንወዳለን እንጂ የምናቀገኘው አንዳች ጥቅም የለንም፡፡ ‹በምን ያሸንፉሃል?› ስለምትለኝም በመታዘዝና በትዕግስት፣ በጾምና በጸሎት፣ በቂም በቀል ንጹሕ በሆነ ልቡና ባለመለያየት ወንድሞቻቸውን ፍጹም በመውደድ፣ ከዚህ ሁሉ ጋራ ትሕትና ከመንፈሳዊ ሥራቸው ሁሉ ትበልጣለችና በፍጹም ሃይማኖት ትሕትናን ቢይዙ ያሸንፉናል፡፡ በመጨረሻም የክርስቶስ ሥጋና ደም የእኛን መርዝ ያጠፋልና እሾሃችንንም ይነቅላልና ያቃጥላል›› አለው፡፡ እዚህ ጋር ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ገድል ላይም ያገኘነውንም ነገር ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እርሷም የዲብሎስን የማሸነፊያ መንገዶች መርምራዋለች፡፡ ቀጥሎ በዝርዝር እንመልከተው፡፡
ሰይጣን የሚሸነፍባቸውን ሦስት ዋና ዋና መንገዶች ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እንደነገራት፡- ‹‹ከዕለታትም በአንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ዕለተ ሞቷን እያሰበች በጣና ባሕር ውስጥ ቆማ ስታለቅስና ስትጸልይ ሣለች ዲያብሎስ በሊቀ ጳጳሳት ተመስሎ እጅግ አስደናቂና ግሩም በሆነ አርአያ ወደ እርሷ መጣ፡፡ እርሷም ልትሰግድለት ወደደች፣ ከኃዘኗ ያረጋጋት ዘንድ ከቅዱሳን አንዱ የመጣ መስሏት ነበርና፡፡ ነገር ግን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ ደረሰና ‹ይህ ሰይጣን እንጂ ጳጳስ ወይም ከቅዱሳን አንዱ አይደለምና አትስገጂለት› ብሎ ወደኋላዋ መለሳት፡፡ ዳግመኛም ‹አሁንም እንደልማድሽ ሂጂና ጠይቂው ማን እንደሆነ ይነግርሻል› አላት፡፡ በዚህን ጊዜ ወደ እርሱ ሂደችና ‹እሰግድልህ ዘንድ አንተ ማን ነህ?፣ ስምህስ ማን ይባላል?› ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም ‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ› አላት፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሷ ጋር እንዳለ አላወቀም ነበርና፡፡ እርሱ በእርሷ ላይ ተንኮል ለመሥራት እንደተራቀቀ ሁሉ እርሷም ነቃችበት ተራቀቀችበት፡፡ ቀጥሎም ‹እንግዲያውስ አንተ ሚካኤል ከሆንክ እስቲ ስለ ጽድቅ ነገር አስተምረኝ› አለችው፡፡ በዚህም ጊዜ ፈጽሞ ተደሰተ-ከዓላማዋ አሳስቶ በእጁ የገባችለት መስሎታልና፡፡ እንዲህም አላት፡- ‹ለምን ሰውነትሽን ታደክሚዋለሽ? ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ ኃላፊ ዓለም ድካም ማረፍ ያስፈልግሻል፣ መጾምና መጸለይስ ለምን ይጠቅምሻል? በባሕርስ ውስጥ ቆሞ መጸለይና ሰውነትን ማድከም ማን አስተማረሽ?› አላት፡፡ በዚያን ጊዜ ‹አንተ የምትለውና መጻሕፍት የሚናገሩት የተለያየ ሆነሳ!?› አለችው፡፡ እርሱም ‹ማነው የለያየን?› አላት፡፡ እርሷም ‹ከአነጋገርህ የተነሣ እኔ ለየኋችሁ› አለችው፡፡ እርሱም ‹እስኪ ልዩነታችንን ንገሪኝ?› አላት፡፡ እርሷም ‹መጻሕፍት የጾመ፣ የጸለየ፣ የለመነም ሁሉ ፍጹም ዋጋውን ያገኛል ይላሉ፡፡ አንተ ግን አትጹሙ፣ አትጸልዩ ትላለህ› አለችው፡፡ ይህንንም ባለችው ጊዜ በእርሷ ላይ ፈጽሞ ተቆጣ፣ እጅግም አድርጎ አስደነገጣት፡፡ ዳግመኛም መለሰችና ‹በምን ትሸነፋለህ?› አለችው፡፡ አሁንም ቁጣውን አወረደባት፡፡ በሦስተኛው ጊዜ ከተቆጣ በኋላ ‹በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች እሸነፋለሁ› ሲል መለሰላት፡፡ ‹አንደኛ ማንኛውም ሰው በዚህ ዓለም በሚኖርበት ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት እንግዳ ተቀብሎ የሚያስተናግድ፤ ሁለተኛው በራሱ ላይ ችግርና መከራ በመጣበት ጊዜ መከራውን ታግሦ የሚኖር፤ ሦስተኛው ቀድሞም ከመሬት የተገኘሁ ነኝ፣ ኋላም ተመልሼ ወደ መሬት እገባለሁ እሞታለሁ እፈርሳለሁ ብሎ በማሰብ ትሕትና የሚሠራና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚያደርግ እርሱ ፈጽሞ ያሸንፈኛል› አላት፡፡ ይህንንም ከተናገረ በኋላ ክንፉን እያማታ ወደ አየር በረረ፡፡ እርሷም ከግርማው የተነሣ ፈጽማ ደነገጠች፣ በመሬትም ላይ ወደቀች፡፡ በዚያን ጊዜ ለጌትነቱ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ቅዱሳት በሚሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣት፡፡ ከዚያም ‹ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ! አይዞሽ አትፍሪው ነገር ግን ወደ ላይ ወደ ሰማይ አቅንተሽ ተመለከቺ› አላት፡፡ ወደ ሰማይ አቅንታ በተመለከተች ጊዜ የዲያብሎስ ክንፉ በሰማይ ላይ ከጽንፍ እስከ አጽናፍ ተዘርግቶ (መላው ዓለምን ሞልቶ) አየች፡፡ ቀጥሎም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹በእኔ በባሕርይ አባቴ በአብ በባሕርይ ሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስ ያላመነ ሊያሸንፈው አይችልም› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹ማንም ሰው ኃጢአት ቢኖርበት ወደቀደመ ኃጢአቱ ባለመመለስ ንስሐ ቢገባ ሥጋዬን ደሜን ቢበላ ቢጠጣ ከወጥመዱ ያመልጣል› አላት፡፡››
ወደ አባ ጳውሊ እንመለስና ከዚህም በኋላ አባታችን ዲያብሎስን ‹‹ከእናንተ የተነሣ የሰው ልጅ ወዮለት›› አለው፡፡ ‹‹ጌታችን ወጥመዳችሁን ያጥፋው፣ ኃይላችሁንም ያድክመው›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹አንተ ሽማግሌ ከእንግዲህ ወዲህ ምንም አልነግርህም ከዚህ ፈጥኜ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ›› እያለ ለመነው፡፡ አባታችንም ‹‹ከዚህ የሚበዛ ብዙ የምጠይቅህ አለኝና አንተ ርኩስ የክፉ ሥራ ምሥጢርህን ጨርሰህ ሳትነግረኝ ከእኔ ትሄድ ዘንድ አላሰናብትህም፡፡ በውኑ ከአዳም ልጆች የምትፈራቸው አሉን?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ከአዳም ልጆች የምፈራቸውም የማልፈራቸውም አሉ›› አለው፡፡ ‹‹እነማንን እንደምትፈራ ንገረኝ? የማትፈራቸውስ እነማን ናቸው?›› ባሉት ጊዜ ዲያብሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹አስቀድሜ ሁሉን ነገርኩህ፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ሥጋውን ለመከራ የሚሰጠውን ሰው እርሱን አፈራዋለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ሥጋውን ለመከራ የማይሰጠውንና ከመከራ የሚሸሸውን አልፈራውም፡፡ ዳግመኛም የቅዱሳንን ዐፅምና ዐፅማቸውን የሚጠብቁትን መላእክት እፈራለሁ፡፡ ቅዱሳኑ ስለክርስቶስ ፍቅር ስለታገሡት ትዕግስትና ስለተጋደሉት ጽኑ ተጋድሎ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ክብር ተዘጋጅቶላቸዋልና በዚያም በተጋደሉበት ቦታ ቃልኪዳን ተቀብለዋልና፡፡ በቦታቸው እንዳንኖር መላእክት ይከለክሉናል፣ ያባርሩናል፣ ኃይላችንም ይደክማል፡፡ እኛም በዚያ ቦታ ትንሽ የኃጢአት ፍርፋሪ እናገኝ ዘንድ ዘወትር ተግተን እንዋጋለን›› አለው፡፡ ዳግመኛም ዲያብሎስ ‹‹በእውነት የቅዱሳንን ምግባርና ትሩፋት ስናይ በእጅጉ እንፈራለን›› አለው፡፡ ‹‹ቅን ኅሊንና፣ ንጹሕ ልብን፣ ትሕትናን፣ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ለመልካም ሥራ መትጋትን ስናይ እንፈራለን፡፡ ይበልጥም የድንግል ማርያም ልጅ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን አቡነ ዘበሰማያትን እንፈራለን›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹የማርያም ልጅ የምትለው ማንን ነው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹አንተን የፈጠረ እርሱ ነው›› አለው፡፡ አባም ‹‹እርሱን ትፈራለህን?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹እባክህ ስሙን እየተራህ አታቃጥለኝ፣ እርሱንማ እንዴት አልፈራው!? እነሆ ኃይሌን አድክሟል፣ ነፍሳትን ፈጽሞ አድኗል፣ ማርኳልና›› አለው፡፡ ደግመኛም ዲያብሎስ ‹‹እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ሰው ሁሉ እንፈራዋለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ቅዱሳን የተናገሯትን ‹ጸሎተ ሃይማኖትንም› በጣም እንፈራለን፣ እርሷ ስትጸለይ በእጅጉ እንደነግጣለን፡፡ ዳግመኛም አንዱ ወንድሙን ‹እኔ በድያለሁና ይቅር በለይ› የሚለውን የይቅርታ ቃል ስንሰማ ደንግጠን ከአጠገቡ እንርቃለን፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ መስቀልና የክርስቶስ ሥጋና ደም ንጹሕ ጸሎት ካለበት ቦታ መቅረብ አይቻለንም፣ እንሸሻለን›› አለው፡፡
አባ ጳውሊም ‹‹የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በምን ትፈትናቸዋለህ?›› ባሉት ጊዜ ዲያብሎስ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ (ይህንን ግን ለዚህ የፌስ ገጽ ምሥጢር እንዲሆን ወደን አላቀረብነውም፡፡) አባ ጳውሊም ‹‹አንተን ያልበደሉህን እነዚህን ሁሉ የተለያዩ ሰዎች እንዲህ የምትፈትናቸው ለምንድነው?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹ሃይማኖታቸው የቀና ሥነ ምግባራቸው ያማረ ከሆነ እንቀናባቸዋለን›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ከሕይወትና ከመልካም ሥራ የተለየህ አንተ ክፉ ባላንጋራ! የኃጢአትና የአመፅ መገኛዋ አንተ ነህና በእነርሱ ላይ ከወዴት ትመጣለች?›› አለው፡፡ ዲያብሎስም ‹‹የክፋትና የዐመፅ ሥራ መገኛዋ እኔ ብሆንም የኃጢአት ፈጻሚዋ እኔ ብቻ አይደለሁም የማቀርብላቸውን የክፋት ሥራ ካልተቀበሉኝ እነርሱን በኃይል ማስገደድ አይቻለኝም፡፡ ነገር ግን በብዙ ዘዴና ተንኮል ሥራዬን እንዲቀበሉ አቀርብላቸዋለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ለመልካም ሥራ መንፈሳዊና አስተዋይ ካልሆኑ በቀር የክፋት ሥራዬን ሳይመረምሩ ይቀበሉኛል›› አለው፡፡
///////////////////////////////
ክፍል ሦስት
‹‹ተዋሥኦተ ቀሲስ አባ ጳውሊ›› (የመጨረሻው ክፍል)...

No comments:

Post a Comment

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ...

በብዙ አንባቢያን የተነበቡ